ምክር ቤቱ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓልን ለማክበር የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለፀ

ሀዋሳ ህዳር 15/2004/ዋኢማ/ – የፊታችን ህዳር 29 የሚከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓልን በድምቀት ለማክበር የሚያስችለውን መሰናዶ ማጠናቀቁን የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አስታወቀ።

የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወርቁ ገብረሥላሴ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ ምክር ቤቱ የክልሉ ሕዝቦች የሠላምና የልማት መሠረት የሆነውን  በዓል በድምቀት ለማክበር የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን አጠናቋል።

በዓሉ በቅድሚያ በክልል ደረጃ ሀዋሳ በመሰባሰብ የዘንድሮ ዓመት የበዓሉ አዘጋጅ ወደ ሆነው የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ መቀሌ ጉዞ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በአከባበር ሂደቱም በክልሉ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች በቀጥታ በበዓሉ ላይ በመሳተፍ ባህላዊ ጭፈራዎችን አልባሳቶችንና የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን ለእይታ እንደሚያቀርቡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙት 83 ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት በደቡብ ክልል የሚገኙ መሆናቸውን የጠቆሙት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ በዚህም መነሻነት የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ለበዓሉ በድምቀት መከበር ልዩ ትኩረት ሰጥተው ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ሕዝቦች ቀደም ሲል በነበሩ ስርዓቶች ይደርስባቸው በነበረው ብሄራዊ ጭቆና የተነሳ በባህላቸው ለመኩራትና በቋንቋቸው ለመጠቀም ይሸማቀቁ እንደነበር ያስታወሱት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ከዚህም በመነሳት ለመብቶቻቸው መከበር በተለያዩ ወቅቶች የጨቋኝ ስርዓቶችን በመቃወም መታገላቸውን ተናግረዋል።   

በተለይም ከደርግ ውድቀት ማግስት ጀምሮ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በነጻነት ለመኖር መብቃታቸውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።