አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2004/ዋኢማ/ – የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽና ባለቤታቸው በኢትዮጵያ፣ በታንዛኒያና በዛምቢያ በቅርቡ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የአሜሪካን ኤምባሲ አስታወቀ፡፡
ኤምባሲው ትናንት እንዳስታወቀው ፕሬዝዳንቱና ባለቤታቸው በሦስቱ የአፍሪካ አገራት ጉብኝታቸውን የሚያደርጉት ከሕዳር 21 ቀን 2004 ዓም ጀምሮ ለአምስት ቀናት ነው፡፡
ጉብኝቱ በጆርጅ ደብሊው ቡሽ ኢንስቲትዩት አማካኝነት በሚተገበረው የግሎባል ሄልዝ ፕሮግራም አማካኝነት የአፍሪካን ሕዝብ ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ እና ባለቤታቸው በአፍሪካ ኤችአይቪ ኤድስን፣ ወባንና ሌሎች በሽታዎችን በመከላከል ረገድ የሚደረገው ጥረት መቀጠል እንዳለበት ያስገነዝባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንዲሁም ባለፉት አስር አመታት በሽታዎችን መከላከል፣ ድህነትንና ፀጥታን በተመለከተ በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ አመርቂ ውጤቶች እንደሚዘከሩ ኤምባሲው አስታውቋል፡፡
ከጉብኝታቸው በተጨማሪም በሴቶች ላይ የሚከሰት የካንሰር በሽታን ለመከላከል አዲስ የተነደፈውን የፒንክ ሪበን ሬድ ሪበን አጋሮች ስልት ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጆርጅ ቡሽ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2001 እንዳስታወቁት አስተዳደራቸውና በአፍሪካ በመከላከል ሊጠፉ የሚችሉ በሽታዎችን ስርጭት መዋጋት ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን አስታውቀው ነበር፡፡
ከ10 ዓመታት በኋላም በፔፕፋር እና ግሎባል ፈንድ አማካኝነት የፀረ-ኤችአይቪ መድሃኒቶችን ያገኙትን 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሕዝብ ጨምሮ በታዳጊ አገራት የሚገኙ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ የኤድስ መድሃኒቶችን አግኝተዋል፡፡
ለዚህም የግል ድርጅቶችና የተለያዩ አገራት መንግስታት እንዲሁም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከባለቤታቸው ጋር በአፍሪካ ለአንድ ሳምንት የሚዘልቅ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያው እንደሚሆን ኤምባሲውን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡