እነመላኩ ፋንታ ለሁለተኛ ቀን ፍ/ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2006 (ዋኢማ) – በፌደራል ስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የመሰረተባቸው እነ መላኩ ፈንታ አና ገብረዋህድ ወልደጊዩርጊስን ጨምሮ የገቢዎች አና ጉምሩክ ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች የጉምሩክ ሰራተኞች አና ባለሀብቶች የክስ መዝገቡ ሲነበብ ውሏል፡፡

 

በፌደራል ስነ ምግባር እና ጸረ ሙሰና ኮሚሽን በግለሰቦቹ ላይ ካቀረበው 3 የክስ መዘገቦች ትናንት ያደሩ ሁለት መዝገቦች ቀርበዋል፡፡
2ቱ መዘገቦች በድምሩ 110 ክሶች የያዙ ናቸው፡፡

 

መዘገቦመቹን ለማየት የተሰየመው የፌደራልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት 31 ሰዎች የተከሰሱበትን የፌደራል የስነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በውድሚያ ያቀረበውን የመዝገብ አንድ ክስ ሂደት በማስቀጠል ችሎቱን ጀምሯል፡፡

 

ችሎቱ በመዘገብ  አንድ ክስ ላይ የሰነድ ማስረጃ ተያያዞ ሊቀርብ ይገባል በሚል በተከሳሽ ጠበቆች የቀረበውን ጥያቄ ጨምሮ ለተጨማሪ የመብት ጥያቄዎች ለጠበቆች ዕድል ሠጥቷል፡፡

 

በ7 ተከሳሾች ላይ የዋስ መብት እንዲከበር ጥያቄ ሲቀርብ፣ የፌደራሉ የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ በበኩሉ በ 3ቱ ላይ ተቃውሞ እንደሌለው የተቀሩት ግን የተከሰሰሱበት የህግ አንቀጽ የዋስ መብት የማያሰጥ ነው በሚል ተቋውሟል፡፡

 

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም በመዝገብ አንድ ሊይ 4 ትዕዛዞችን ሰጥቷል፡፡
በዚህም መሰረት ተከሳሶች የቀረበባቸውን ክስ ማንኛውንም ማስረጃ የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተከብሮ እስከ ጥቅምት 19/2006 እንዲደርሳቸው፣ የማስረጃ መግለጫን በተመለከተ ማስረጃው ከቀረበ በኋላ እንዲወሰን ፣የዋትና ጥያቄ ካቀረቡት መካከልም የተከሰሱበት የወንጀል ህግ ድንጋጌ ከ 10 ዓመታት በታች የሚያስቀጣ በመሆኑ 20ኛ፣ 21ኛ እና 24ኛ ተከሳሾች በ15 ሺህ ብር ዋስ መብታቸው እንዲከበር ፣በመዝገቦቹ ሊቀርብ ያልቻሉ ተከሳሾችንም የፌደራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ሰርቪላንስና ክትትል ቡድን እንዲያቀርብ አዟል፡፡

ከዚህ በማስቀጠልም ችሎቱ በ17 ክሶች 10 ሰዎች የተከሰሱበትን ባለ 41 ገጽ 2ኛ  የክስ መዝገብ  በ93 ክሶች 24 ሰዎች የተከሰሱበትን ባለ 74 ገጽ 3ኛ የክስ መዝገቦች በንባብ ተሰምቷል፡፡

በሁሉም መዘገቦች የቀድሞ የገቢዎች ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታና ምክትላቸው ገብረዋህድ ወልደጊዩርጊስ በተናጠልና በቡድን በርካታ ክሶች ቀርበውባቸውል፡፡

ባለስልጣናቱ በስልጣናቸው ተጠቅመው የአሰራር ስርዓቶችን በመጣስና ከተለያዩ የግል ድርጅቶች ጋር በጥቅም  በመገናኘት መንግስት ማግኘትት የነበረበትን ገቢና ከፍተኛ የህዝብ ሀብት አሳጥተዋል ብሏል የክሱ ዝርዝር፡፡

ከክሱ ዝርዝሮች መካከል አሰራሮችንና አዋጆችን በመጣስና ህግ ወጥ ኮሚቴ በማቋቋም አቶ መላኩ ፋንታ ከሃዋዝ አግሮ ቢዝነስ ከተባለ ኩባንያ መሰብሰብ የነበረበት ከ20 ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺ ብር በላይ ግብርና ታክስ እንዳይሰበሰብ ማድረጋቸው፤

ያማት ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት በኦዲት እንዲከፍል የተወሰነውን ከ48 ሚሊየን 4መቶ 40ሺ ብር የተጨማሪ እሴት ታክስ ና የገቢ ግብር ወደ 34 ሚሊዮን ዝቅ እንዲል ማድረጋቸው ፤በህጋዊ ግብይት ከሚያገኙት በላይ 659 ካሬ ሜትር ቦታና ባለ 2ፎቅ ህንፃ ከሶስት ሚሊዮን ብር  በላይ የገንዘብና የሀብት ንብረት አፍርተው መገኘታቸው ፤ በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ይጠቀሳል፡፡

አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ ሃዋዝ አግሮ ቢዝነስ በአዳማ ገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ሊከፍል የሚገባው የተጨማሪ እሴት ታክስ ና የትርፍ ግብር ብር 22 ሚሊዮን 3መቶ 79ሺ 145 የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ እስካሁን እንዳይሰበሰብ ማድረጋቸው፣ከሼባ ስቲል ሚልስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሰብሰብ የነበረበት 1ሚሊዮን 487ሺ 9መቶ78 ከ40ሳንቲም  በተጭበረበረ ደብዳቤና ህገወጥ  አሰራር እስካሁን እንዳይሰበሰብ ማድረጋቸው፣ከሌሎች ተካሳሾቸ  ጋር በማበር አለማ ፋርምስ፣የሸዋ  ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ሪፍቲ ቫሊ ሆቴል፣ስሪ ኤስ የግል ኩባንያ፣ይሳለሙሽ የዱቅት ፋብሪካ ፣ሙባረክ ሰይድ ሸቀጣሸቀጥ ንግድ ድርጅት የተባሉ የንግድ ተቋማት ሊከፍሉት የሚገባ ከፍተኛ መጠን ያለው  ግብርን፣ተጨማሪ እሴት ታክስና ተያያዥ ገቢዎች እንዲቀነሱና እንዳይሰበሰቡ ማድረጋቸው፤አቶ ገብረዋህድ  በድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሱሁራ 571 የተባለ የግል ማህበር እንዲከፍል የተወሰነበትን የትርፍና የተጨማሪ እሴት ታክስ ግብር 91ሚሊዮን 7መቶ47ሺ325ብር እንዲከፍል የሚወሰዱ እርምጃዎችን በማዘግየት እንዳይሰበሰብ ማድረጋቸው ከተዘረዘሩባቸው ክሶች መካካል ይጠቀሳሉ፡፡

በአጠቃላይ በ2ኛው መዝገብ ተከሳሽን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች ለጠበቃቸው ሊከላከሉት የሚገባውን የመንግስትና የህዝብ ጥቅም በከፍተኛ ሁኔታ በሚጎዳ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በ3ኛው መዝገብ በቀረበው ክስም 1ኛ ተከሳሽ አቶ መላኩ ፈንታና 2ኛ ተከሳሽ አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ ከ2001 አራጣ አበዳሪዎችን ለህግ ለማቅረብ በተደረገው እንቅስቃሴ 10ኛ ተከሳሽ አቶ ከተማ ከበደ አራጣ አበዳሪ መሆናቸውን እያወቁ ለህግ እንዳይቀርቡ ማድረጋቸው፣እንዲሁም 11ኛው ተከሳሽ አቶ ከተማ ከበደ ለሆቴል አገልግሎት ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸውን እቃዎች ለሌላ አገልግሎት አውለው ለህግ እንዳይቀርቡና በዚህም ለመንግስት ገቢ መደረግ የነበረበት 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ለሌላ አላማ ሲውል አውቀው ዝም ማለታቸውንና በጥቅም ለተሳሰሯቸው ባለሃብቶች መተባባራቸው ተዘርዝሯል፡፡

ከ1999 እስከ 2000 የስሚንቶ  እጥረት ለማረጋጋት ከቀረጥ ነጻ የሚገባውን ሲሚንቶ ለ3ኛ ወገን በማስተላለፍና ለመንግስት ገቢ መሆን የነበረበትን  ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ በማሳጣትም 1ኛ፣2ኛ፣8ኛ፣9ኛ፣16ኛ፣17ኛና 24ኛ ተከሳሾች ተጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ሂደት ተሳትፈዋል የተባሉት ጌት አስ ትሬድንግ ፣ነጻ ትሬዲንግ፣የኮሜት ትሬዲንግ ኩባንያዎችና በትራንዚተሮችና በትራንስፖርት ባለንብረቶች ላይ ክስ እንዳይመሰረት እንዳደረጉ፣24ኛ ተከሳሽ ወልደስላሴ ወልደ ሚካኤል ደግሞ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስርያቤት የነበራቸውን ሃላፊነት አለአግባብ በመጠቀምና ወደ ሁለተኛ ተከሳሽ ቢሮ በተደጋጋሚ በመሄድ በሲሚንቶ  ማጭበርበር ጥቆማዎች ላይ ሰዎችን አስቀርቦ በመመርመር የሌላ ሰው ነው ብለው እንመሰክሩ ማድረጋቸው ተዘርዝሯል፡፡

በዚህ መዝገብ 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ፓኬጅ ትሬዲንግ ለመንግስት ገቢ ማድረግ የነበረበት  ከ2ሚሊዮን 88ሺህ ብር በላይ እንዳይሰበሰብ በማድረግና በሌሎች በርካታ የሙስና ወንጆሎች ተሳታፊ ስለመሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

ሌሎች 22 ተከሳሾች በተለያዩ የቀረጥ የገቢ ግብርና ተያያዥ ተግባራት ከፍተኛ የህዝብና የመንግስት ሃብት አለአግባብ እንዲመዘበር አድርገዋል ይላል መዝገቡ፡፡

ችሎቱ 2ቱን የክስ መዝገብ በንባብ ከሰማ በኋላ ሂደቱን ለማስቀጠልና ክርክሮችን ለመስማት ለነገ ጥቅምት 13/2006 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ (ኢሬቴድ)