የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በቅርቡ የሚካሄደውን አለም አቀፍ የቤተሰብ እቅድ ጉባኤ ትኩረት ሰጥተው እንዲዘግቡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2006/ዋኢማ/ -በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን 3ኛውን አለም አቀፍ የቤተሰብ እቅድ ጉባኤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተገቢውን ሽፋን በመስጠት ህብረተሰቡ ማግኘት ያለበትን ግንዛቤ እንዲያገኙ ማስቻል እንደሚገባቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ኢማኖ ሰሞኑን በናዝሬት ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ እንደገለፁት፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በጉባዔው ወቅት የሚነሱ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመዘገብ ህብረተሰቡ እንዲማርበት ማድረግ ይገባቸዋል።

ኢትዮጵያ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ለማዳረስ በርካታ ስራዎችን መስራቷን ያስታወሱት አቶ አህመድ በዚህም 3ኛውን አለም አቀፍ የቤተሰብ እቅድ ጉባዔ እንድታዘጋጅ ተመርጣለች ብለዋል።

በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹም የሀገራቸውን በጎ ገፅታ ከመገንባት አንፃር የሚጠበቅባቸውን መስራት እንደሚገባቸው አሳስበው፤ በተለይም በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ምርጥ ተሞክሮዎችን ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ በማስተዋወቅ በኩል የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት።

በሀገሪቱ ከ20 ዓመት በፊት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት 14 በመቶ እንደነበረ ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ 29 ነጥብ 9 በመቶ ማድረስ መቻሉን አቶ አህመድ ተናግረው፤ በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት አመታትም ሽፋኑን ወደ 65 በመቶ ለማድረስ የተለያዩ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በጉባዔው ላይ ከ3 እስከ 4ሺ የሚሆኑ የተለያዩ ሀገራትን የሚወክሉ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ፖሊሲዎች አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የተለያዩ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ምርጥ ተሞክሮ ያላቸው ግለሰቦች እንደሚካፈሉ ነው አቶ አህመድ የገለፁት።
በጉባዔው ላይም ከ1ሺ 300 በላይ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን፤ የስእል ኤግዚቢሽንና የመስክ ጉብኝት እንደሚካሄድ ነው የተጠቆመው።

እንዲሁም በግለሰቦች፣ ድርጅትና በሀገር አቀፍ ደረጃ በቤተሰብ እቅድ ላይ መልካም ስራ ለሰሩ ሽልማት እንደሚበረከትም ጠቁመው፤ የመገናኛ ብዙሃንም በጉባዔው ወቅት የሚከናወኑ ተግባራትን በመከታተል ለህብረተሰቡ በማድረስ በኩል የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ግዴታ መወጣት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።
የመጀመሪያው የቤተሰብ እቅድ ጉባዔ በካምፓላ የተካሄደ ሲሆን፤ ሁለተኛው በሴኔጋል ሶስተኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ከህዳር 3 እስከ 5 የሚካሄድ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን በእጥፍ በማሳካቷ ይህንን ጉባኤ እንድታዘጋጅ መመረጧንም አቶ አህመድ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።