በአፍሪካ ኢንቨስት የሚያደርግ ባለሀብት ውጤታማ ይሆናል፡-ጠ/ሚ ኃይለማርያም

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2006 (ዋኢማ) – ሰፊና ያልታረሰ መሬት እንዲሁም ርካሽ የሰው ጉልበት ባለባት አፍሪካ ኢንቨስት የሚያደርግ ኩባንያና ባለሀብት በንግዱ ዘርፍ ውጤታማ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ፡፡

በዴንማርክ ኮፐን ሀገን በተደረገው የአለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ፎረም ላይ የተሳተፉት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማርያም ደሳለኝ  አፍሪካ ከኢስያ ቀጥሎ በከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡

የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚን በማጠናከር አፍሪካ ወደ ኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ በምታደርገው ሽግግር እድገቱ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን እንሰራለንም ብለዋል፡፡

በአለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ፎረም የተገኙት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በንፁህና በታዳሽ የሃይል ምርት ግንባታ ቢሰማሩ ኢትዮጵያ ግማሽ መንገድ ተጉዟ ትቀበላቸዋለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማርያም አፍሪካ አሁን የምትከተለው የምጣኔ  ሃብታዊ እድገት መሰላልም ለአለም አቀፍ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት የበኩሉን ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

እንደ ኢሬቴድ ዘገባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፓብሊሲቲ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው ረዳ ኢትዮጵያ በፎረሙ የተጋበዘችው አሁን ካላት የአረንጓዴ ልማት ውጤታማነት መሆኑን ገልፀዋል፡፡