ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ ያለውን የሆስፒታል ቁጥር ወደ 800 ለማድረስ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2006/ዋኢማ/ – በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የጤናውን ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ የሆስፒታል ቁጥርን ወደ 800 ለማድረስ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እየሰራ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ኢማኖ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በሀገሪቱ ያለውን ህክምና በማሳደግና በማሻሻል ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ ሀገር እንድትሆን ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት 3ሺ 245 ጤና ጣቢያ፣ 16 ሺ 048 ጤና ኬላና 229 ሪፈራል ሆስፒታሎች በሀገሪቱ ውስጥ እንዳለ ገልፀው፤ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ይህንን ቁጥር በማሳደግ ሀገሪቱ ከሜዲካል ቱሪዝም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበትን መንገድ ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ከማካሄዷም በተጨማሪ በየአመቱ የቱሪስት መስህቦችን ለመጎብኘት ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ እንግዶች ቁጥር እየጨመረ መምጨጣቱን የጠቆሙት አቶ አህመድ፤ ቱሪስቶቹ ከጉብኝታቸው በተጨማሪም ህክምና ለማግኘት ሲሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

እቅዱን ለማሳካትም 175 አዳዲስ ሆስፒታሎች በግንባታ ላይ እንዳሉ ጠቁመው፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች 58 ሆስፒታል፣ በኦሮሚያ 56፣ በአማራ 55፣ ቤንሻንጉል አራት፣ አፋርና ድሬዳዋ አንድ አንድ ሆስፒታሎች ግንባታቸው እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ሆስፒታሎች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገቡ ከ1 ሚሊየን እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ወገኖች አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚችሉ አቶ አህመድ አመልክተዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመትም አራት ሆስፒታሎች ተጠናቀው ስራ መጀመራቸውን ገልፀው፤ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉ ያለውን የባለሙያ ችግር ለማስወገድም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ባለሙያዎችን በዘርፉ የማብቃት ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ አህመድ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።