የኢህአዴግ ምክር ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ ተፈፃሚ እንዲሆን እንደሚሰራ የጋምቤላ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህዴን) አስታወቀ፡፡
በአገሪቷ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና የተጀመረው ልማታዊ ጉዞ እንዲጠናከር ችግሮችን በፍጥነት በመለየት ዘለቄታዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ የኢህአዴግ ምክር ቤቱ መወሰኑን ንቅናቄው አስታውሷል፡፡
ጋህዴን በኢህአዴግ የተነደፉ የልማትና የዲሞክራሲ አቅጣጫዎችን በመከተል ለተሻለ ውጤት እየተጋ እንደሚገኝ የንቅናቅው ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦኬሎ ኡማን ለዋልታ ገልፀዋል፡፡
በቅርቡ የግንባሩ ምክር ቤት ውስጣዊ ችግሮቹን በመፈተሸ ያስተላለፈውን ውሳኔ ጋህዴን በሙሉ ልብ በመቀበል የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ ይሰራል ብለዋል፡፡
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተዘጋጁ ህዝባዊ መድረኮች ላይም ህዝቡ ውሳኔውን በማድነቅ ለተፈፃሚነቱ የበኩሉን ለመወጣት መዘጋጀቱን መግለፁን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ በተለይም ሠላም በማስፈን ረገድ ህዝቡ በንቃት እንደሚሳተፍ መናገሩን አቶ ኦኬሎ አስረድተዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ለግጭት መንስዔ የሆኑ ጉዳዮች በሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኙ የተላለፈው ውሳኔም የሚደነቅ እንደሆነ ነው አቶ ኦኬሎ የተናገሩት፡፡
ከመልካም አስተዳደር እጥረት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘለቄታዊነት ለመፍታትና የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ግንባሩ በትኩረት ለመሄድ ቆርጦ መነሳቱን ጋህዴን አስታውቋል፡፡ ጋህዴንም እንደ አጋር የሚበቅበትን ይወጣል ነው ያሉት፡፡
የጋምቤላ ክልል ከጎረቤት አገር ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ሠላምን በማስጠበቅ በኩል ህዝቡና የክልሉ መንግስት ከምንጊዜውም በላይ በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት ከደቡብ ሱዳን ወደ ክልሉ ሰርገው በመግባት በሰው ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ያደረሱ፣ህፃናትን አግተው የወሰዱና ከብቶችን የዘረፉ ፀረ ሠላም ቡድኖች ዓይነት ተመሳሳይ ህገ ወጥ ድርጊት እንዳይሞከር ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ህገ ወጦችን በመከላከልና በመጠቆም፣ ህግ ፊት ቀርበው ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በማድረግ በኩልም ህዝቡና የክልሉ መንግስት በትኩረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተመልክቷል፡፡