በኢሬቻ በዓል ላይ የ52 ሰዎች ህይወት ማለፉን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ

በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ ምክንያት የ52 ሰዎች ህይወት ማለፉን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ገለፀ።

የክልሉ መንግስት በዛሬው የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ የተከሰተውን ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ “የክልሉ ህዝብ በዓሉን ለአለም አምረው እና ደምቀው በሚገባ ለማሳየት ከፍተኛ ጉጉት እና ምኞት የነበረው በመሆኑም በዚሁ ምክንያት በተለያዩ የክልላችን አካባቢዎች እና የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም የተለያዩ አለምአቀፍ እንግዶች የታደሙበት ሆኖ ሳለ ለባህላችን እና ለህዝባችን ምንም ደንታ የሌላቸው ኃይሎች በጠነሰሱት እኩይ ሴራ ምክንያት ሁከት እና ብጥብጥ ተፈጥሯል” ብሏል።

መንግስት ከፍተኛ ትግስት እና ጥንቃቄ ያደረገ ማድረጉን የገለፀው መግለጫው “የጥፋት ኃይሎች ስርዓቱ በአግባቡ እንዳይፈፀም ለህዝቡ እና ለአባገዳዎች ምንም አይነት እክብሮት ሳይሰጡ እንዲስተጓጎል አድርገውታል” ነው ያለው።

በዚህም በተፈጠረ መገፋፋት እና መረጋገጥ ምክንያት ዜጎች ውድ ህይወት መጥፋቱን አስታውቋል።

ይህም ሁኔታ ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ምክንያት እንጂ በአንዳንድ ማህበራዊ ድረ-ገፆች እንደሚሰራጨው የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ምክንያት እንዳልሆነ በአካባቢው የተገኘው ህዝባች ምስክር መሆኑንም ነው የገለፀው።

በጥፋት ኃይሎች እኩይ ተግባር ህይወታቸውን ላጡት ዜጎች መንግስት ጥልቅ ሀዘን ይሰመዋል ያለው የክልሉ መንግስት፥ ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው የክልሉ ህዝቦች መፅናናትን ተመኝቷል።

ከተጎጂ ቤተሰቦች ጎን በመቆምም አስፋላጊ ሆኖ የተገኘውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም አስታውቋል።

መንግስት እንደትላንቱ ሁሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን ዛሬም የገዳ ስርዓት በአለም ዘንድ እንዲታወቅ ለማድረግ የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ብሏል።

ይህንን የህዝቡን ጥቅም የሚጎዳ እና ከባህል ውጪ የሆነ አሳዛኝ ድርጊት ህዝቡ አምርሮ እንዲያወግዝም ክልላዊ መንግስቱ ጥሪ አቅርቧል ።