ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ በግብርና፣ ኢንዱስትሪና ባቡር ልማት ሥራዎች በጋራ ለመሥራት ተስማሙ፡፡
ሳውዲ አረቢያን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከንጉስ ሰልማን ቢን አብዱልአዚዝ ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮ ሳውዲን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለማጠናከር መክረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በተለይም የሳውዲ ባለሃብቶችና የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።
ሀገራቱ በመሠረተ ልማት ትስስር በጋራ ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ገልፀዋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ የሰላም ሁኔታ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮችም ሀገራቱ በጋራ ለመስራት መምከራቸውን የገለጹት ደግሞ በሳውዲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አሚን አብዱልቃድር ናቸው ፡፡
የሳውዲ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በስፋት ከተሰማሩ የተለያዩ ሀገራት ባለሀብቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡