በብልሹ አሰራር በተዘፈቁ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠ/ሚ ኃይለማርያም አስታወቁ

ስልጣንን አለአግባብ በተጠቀሙና በብልሹ አሰራር በተዘፈቁ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ ።

በኢህአዴግ ምክር ቤትና ስራ አስፈፃሚው በህዝቡ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታትና ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌን ለማስወገድ የተቀመጠው በጥልቀት የመታደስ አቅጣጫ በመግባባትና በጥሩ መንፈስ እየተካሄደ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

እስካሁን የተወሰዱት እርምጃዎች ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስልጣናቸውን አላግባብ በተጠቀሙና በብልሹ አሰራር በተዘፈቁ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በክልሎች እና ወደ ታች ባሉ የመንግስት መዋቅሮች በአዲስ መልክ የማደራጀት ስራው በተገቢው መንገድ እየተከናወነ እንደሆነም አስረድተዋል።

ህዝቡ የተዛቡ አመለካከቶችን ወደ ጎን በመተው አገራዊ አንድነትን የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት የተፈጠረበት፣ በአገሪቱ የነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች የተወገዱበትና አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማሕበረሰብ ለመፍጠር መሰረት የተጣለበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በዓሉ አገራዊ አንድነትን የበለጠ የሚጎለብትበት እንዲሁም ሕብረ ብሔራዊነት የሚጠናከርበት ነውም ብለዋል።

የተከሰተውን ሁከት ለማስቆም ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሃገሪቱን ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለሱንና ለውጤቱ መገኘትም የህዝቡ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።

በሃገሪቱ የተከሰተውን ሁከት ለማስቆም ተግባራዊ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ እንዳላሳደረም ገልጸዋል(ኢብኮ ) ።