መንግስት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እምቅ ሀብቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል- ጠቅላይ ሚኒስትር

መንግስት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያለውን እምቅ ሀብት ህብረተሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዋና መቀመጫ አሶሳ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ትናንት ውይይት አድርገዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የዋጋ ንረት፣ ክልሉ ያለውን ሀብት ህብረተሰቡ እየተጠቀመ እንዳልሆነና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት የተሟላ አለመሆኑን የተመለከቱ ሀሳብና ጥያቄዎች ከውይይቱ ተሳተፊ የክልሉ ነዋሪዎች ተነስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህብረተሰቡ ባነሳቸው ጉዳዮች ላይ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ዶክተር አቢይ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ መንግስት ክልሉ ያለውን እምቅ ሀብቶችና ጸጋዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በሙያተኛ በመታገዝ ይሰራል።

በማንጎ፣ በቀርከሃ፣ በከሰል ድንጋይና ሰሊጥ ላይ ያለውን ሀብት ህብረተሰቡን መጥቀም አለባቸው የሚለው ሀሳብ በመንግስት በኩል ተቀባይነት እንዳለው ገልጸዋል።

መንግስት በመሰረተ ልማት በተለይም የመንገድ ግንባታ የተጓተተበትን ምክንያት በማጣራት አስፈላጊውን መፍትሔ እንደሚሰጥ ነው ዶክተር አቢይ ያስታወቁት።

ጊዜና ወቅት እየጠበቁ በተለያዩ ምርቶች የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ህብረተሰቡን የሚጎዱ አካላት በሂደት የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸው እንደማይቀር በማስገንዘብ ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አስጠንቅቀዋል።

"ነጋዴዎች ትርፍ ይገባችኋል ነገር ግን አግባብ ያልሆነ ትርፍ አይገባችሁም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የንግዱ ማህበረሰብ ለፍትሐዊ፣ሰላማዊና ጤናማ የንግድ ስርአት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዲፈታ ከተቋማቱ ጋር በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫ ይቀመጣል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ያነሳቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና የልማት ጉዳዮች መንግስት በእቅዱ ውስጥ በማካተት ተግባራዊ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ያሉባትን ችግሮች መፍታት የመንግስት ስራ ብቻ እንዳልሆነና ሁሉም የሚመለከተው አካል ለአገሪቷ ልማትና ሰላም በጋራ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በመዘዋወር ከህዝብ ጋር ባደረጉት መተዋወቅና ውይይት በአገሪቱ ያሉትን ችግሮች በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ምክክር አድርገዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት በጥናት ላይ የተደገፈ የመፍትሄ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን መጠቆማቸው ይታወሳል-( ኢዜአ) ።