ጄኔራል ሳሞራ የኑስ እጅግ ከፍተኛ የኒሻን ሽልማት ተበረከተላቸው

ጠቅላይ ኢታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ የአገሪቷ እጅግ ከፍተኛ የኒሻን ሽልማት ተበረከተላቸው።

ጄኔራል ሰሞራ ይህንን ከፍተኛ የክብር ሽልማቱን ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እጅ ተቀብለዋል።

የክብር ሽልማቱ የተበረከተላቸው ከተዋጊነት እስከ አዋጊነትና እስከ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታ ማዦር ሹምነት ድረስ አገራቸውን በትጋትና በታታሪነት በማገልገላቸው መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም በመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ባስገኙት ውጤት፣ባሳዩት የአመራር ብቃትና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ላበረከቱትም የላቀ አስተዋጽዖ ሽልማቱ ተበርክቶላቸዋልነው ያሉት።

ሰራዊቱ ለሕዝብ የወገነና ከብረት የጠነከረ ሕገመንግሥታዊ እምነት እንዲኖረውም በዲስፒሊን የታነጸ እንዲሆንና በውትድርና ሳይንስ የታጠቀ እንዲሆን ጄኔራል ሳሞራ ሰርተዋልብለዋል።

ከሠራዊት ምስረታ ጀምሮየሠራዊቱን አባላት በሂደት በመገንባት ዛሬ የመከላከያ ሰራዊት አሁን ለደረሰበት ደረጃም የእርሳቸው አስተዋጽዖ የጎላ በመሆኑም ምስጋና ይገባቸዋልብለዋል።

በዚህም በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 71 ንዑስ አንቀጽ 5 መሰረት በደመቀ ሥነሥርዓት ዛሬ ማምሻውን በብሔራዊ ቤተመንግሥት የኒሻን ሽልማቱ ለጄኔራሉ ተበርክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በዚሁ ወቅት ጄኔራል ሰዓረ መኮንን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አድርገው ሾመዋል።

ቀደም ሲል ወታደራዊ ማዕረጋቸው ተነጥቆባቸው የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ እና ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌም ማእረጋቸው ተመልሶላቸው ከሙሉ የጡረታ ጥቅማጥቅም ጋር እንዲሰናበቱ ወስነዋል።

ጄኔራል ሳሞራ ከተዋጊ ወታደርነት እስከ ጠቅላይ ኤታሞዦር ሹምነት 42 ዓመታት አገልግለዋል። ጄኔራል ሳሞራ የአራት ልጆች አባት ናቸው።