3ኛው ሀገር አቀፍ የእግረኞችና የብስክሌተኞች ቀን ተከበረ

“ከጳጉሜን እስከ ጳጉሜን እንደርሳለን!” በሚል 3ኛው ሀገር አቀፍ የእግረኞችና የብስክሌተኞች ቀን በአዲስ አበባ፣ ሀረሪ፣ ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሀዋሳ፣ ገላን፣ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በትላንትናው እለት በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በአዲስ አበባ  ከተማ በተካሄደው መድረክ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የህዳር ወር ቆሻሻን የማስወገድ የቆየ ልማዳችንን በየአካባቢያችን በመተግበር መንገዶቻችንን እና ከተሞቻችንን ለእግረኞችና ለሳይክል ተጠቃሚዎች ንጹሕ በማድረግ ተጠቃሚው ለትራፊክ አደጋ እንዳይጋለጥ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ሚኒስትሯ ህብረተሰባችን በቀጣይም አመቱን ሙሉ ወር በገባ በመጨረሻው እሁድ በሚከናወነው የእግረኞችና የብስክሌተኞች ቀን የንቅናቄው አካል በመሆን በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰተውንና በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ዉድመትን በጋራ ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ሚኒስቴሩ የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂን በመተግበር  የሳይክልና የእግረኞች መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋትና የህብረተሰቡ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ዕለቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ውድ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የህሊና ጸሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን፣ የእግር ጉዞ፣ በብሔራዊ መዝሙር፣  በህጻናት መዝሙር እና በበርካታ ብስክሌተኞች እንቅስቃሴ ታጅቦና በተለያዩ ሁነቶች ተከብሮ መዋሉን ከትራንስፖርት ሚኒሰቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በመጨረሻም ሚኒስትሯ በመላው የሀገሪቱ ከተሞች ይህንን ፕሮግራም በተመሳሳይ ሰዓት በማካሄድ ያሉ ዜጎችን አመሰግነዋል።