ባለፉት አራት ወራት ከማዕድን ዘርፍ 269.1 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ

ባለፉት አራት ወራት ከማዕድን ዘርፍ 269 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የነዳጅና ማዕድን ሚኒስቴር አስታወቋል፡፡

የነዳጅና ማዕድን ሚኒስትር ኢ/ር ታከለ ኡማ በማዕድን ዘርፍ አፈፃፀምና ቀጣይ እቅዶች ዙሪያ ከክልል የማዕድን ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ባለፉት አራት ወራት 3 ሺህ 602.8 ኪሎግራም ወርቅ ለውጭ ገበያ ቀርቦ 265.8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

ከጌጣጌጥ ማዕድናት ደግሞ 3.215 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱ ተነግሯል።

በእቅድ የተያዘው የወርቅ ምርት የተከለሰ ሲሆን፣ በተሻለ መንገድ ኢኮኖሚውን መደገፍ በሚያስችል መልኩ ምርቱን ለመጨመር ከክልል አመራሮቹ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

በቀጣይም ዘርፉን ዘመናዊ መልክ ለማስያዝ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተገለጸ ሲሆን፣ የማዕድን ፈቃድ ተሰጥቷቸው በአግባቡ እየተጠቀሙበት ያልሆኑ ተቋማት ላይ መወሰድ ስላለበት እርምጃ በተመለከተ ውይይት መደረጉን ከነዳጅና ማዕድን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡