3 ሐሰተኛ የክሮም ማሰሻ ኤክስቴንሽኖች ከ1.5 ሚሊዮን ጊዜ በላይ በተጠቃሚዎች ላይ በግዳጅ መጫናቸው ተገለጸ


ታኅሣሥ 17/2016 (አዲስ ዋልታ) በምናባዊ የግል አውታረ መረብ (Virtual Private Network-VPN) መልክ ለጥቃት ዓላማ የተፈበረኩ ሦስት ሐሰተኛ የክሮም ማሰሻ ኤክስቴንሽኖች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጊዜ በላይ በተጠቃሚዎች ላይ በግዳጅ መጫናቸው ተገለጸ።

በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የተሰማራው “ሪዝንላብስ” የተባለው ኩባንያ እንደገለጸው በቪ.ፒ.ኤን መልክ ራሳቸውን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጊዜ በላይ በኃይል እንዲጫን ያደረጉት እነዚህ ሦስት ሐሰተኛ የክሮም ድር ማሰሻ ኤክስቴንሽኖች ድር ማሰሻዎችን (web browser) የመጥለፍ፣ በበይነ መረብ የቀጥታ ግብይት ወቅት ለደንበኞች ማበረታቻ ከሻጮች የሚመለሱ ገንዘቦችን የመመንተፍና የመረጃ ስርቆት መሣሪያ ሆነው የማገልገል ዓላማ ያላቸው ናቸው።

የተሰራጩት ደግሞ እንደ ግራንድቴፍት አውቶ፣ አሳሲንስ ክሪድና ዘ ሲምስ 4 በመሳሰሉ ቶረንት ላይ በሚገኙ ታዋቂ የጨዋታ መተግበሪያዎች ላይ በድብቅ በተጫኑ ኢንስቶለሮች አማካኝነት ነው ተብሏል።

የሳይበር ደህንነት ኩባንያው ሪዝንስላብ ሀሰተኛ የክሮም ድር ማሰሻ ኤክስቴንሽኖችን ተከታትሎ ከደረሰባቸው በኋላ ግኝቱን ለጉግል በማሳወቁ ጉግል ከክሮም ዌብስቶር እንዲነሱ ቢያደርግም እስኪወገዱ ድረስ በቆዩባቸው ጊዜያት ራሳቸውን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጊዜ በላይ እንዲጫኑ አድርገው መገኘታቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ከ100 በላይ በበይነ መረብ የቀጥታ ግብይት ወቅት ለደንበኞች ማበረታቻ ተመላሽ ገንዘብ የሚሰጡ “ካሽባክ” (Cash back) ኩባንያዎችን ዒላማ ያደረገውና በተጨማሪም ማሰሻዎችን የመጥለፍና ጥብቅ የግልና የኩባንያ መረጃዎችን የመስረቅ ዓላማ የነበረው እንዲህ ዓይነቱ የሐሰተኛ ቪ.ፒ.ኤን የክሮም ኤክስቴንሽን ጥቃት፤ የተጠቂውን ምንም ዓይነት ተሳትፎ የማይፈልግና ራሱን በእስገዳጅ ሁኔታ የሚጭን አደገኛ የበይነ መረብ ጥቃት መሆኑን ኩባንያው አስገንዝቧል።

ይህም የድር ማሰሻ (web browser) የሳይበር ደህንነት በከፍተኛ ደረጃ ለስጋት ያጋለጠ ከመሆኑም ባሻገር ለመከላከልም አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ያመላከተው ሪዝንስላብ ያም ሆኖ እንዲህ ዓይነቱን ጥቃት ለመከላከል ተጠቃሚዎች በድር ማሰሻቸው ላይ የሚጫኑ (install የሚደረጉ) ኤክስቴንሽኖችን ደህንነት በየጊዜው ማረጋገጥና በሌሎች ማሰሻዎች አማካኝነት ከዚህ ቀደም አንዳች ዓይነት የደህንነት ሪፖርት ቀርቦባቸው ወይም አልቀረበባቸው እንደሆነ ማወቅ የሚጠበቅባቸው መሆኑን አመልክቷል።