30ኛው የምርምር ጉባዔና የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን እየተካሄደ ነው

30ኛው የምርምር ጉባዔ

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) 30ኛው የምርምር ጉባዔና የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት መካሄድ ጀምሯል፡፡

ለ29 ዓመታት ከውጭና ከሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራንን በመጋበዝ የምርምር ጉባዔ ሲያካሄድ የቆየው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 3 ዓመታት በኮቪድ 19 እና በሀገሪቱ በተከሰተው አለመረጋጋት ሳቢያ ጉባዔውን ማካሄድ ሳይችል ቀርቷል፡፡

ሆኖም ከሦስት ዓመታት በኋላ ዘንድሮ 30ኛውን የምርምር ጉባዔ “ምርምር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ለመልሶ ማቋቋምና እድገት” በሚል መሪ ቃል ከዛሬ ግንቦት 17 እስከ ግንቦት 19/2014 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት ማካሄድ ጀምሯል፡፡

በምርምር ጉባዔው በዋነኝነት በተከሰተው ጦርነትና በሌሎች ዓለም ዐቀፍ ፈተናዎች ጉዳት የደረሰበት ኢኮኖሚ እንዲያገግም፣ በወራሪው የሽብር ቡድን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ማቋቋም ላይ ትኩረት ያደረጉ የምርምርና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ቢኒያም ጫቅሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው 11 የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቶችን ቀርፆ የተለያዩ የመልሶ ማልማት ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱም ተጠቅሷል፡፡

በጉባዔው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዲኤታው ንጉሱ ጥላሁንን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሳሙኤል ሓጎስ (ከጎንደር)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW