ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መልዕክት ላኩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ዛሬ መልዕክት ልከዋል።

የኤርትራ  መንግሥት ከፍተኛ ልዑክ ቆይታን በተመለከተ   ዛሬ መግለጫ የሰጡት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንደገለጹት የሁለቱ አገራት  በመሪዎች ደረጃ በቅርቡ ውይይት ያደርጋሉ።

አዲስ አበባ ላይ ከኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ ቡድን ጋር የተደረገው ውይይት ለሁለቱ  አገራት ሰላም ምቹ መደላድል የፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።

 የኤርትራ የመንግሥት  ከፍተኛ ልዑክ  በትናንትናው እለት የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ ለማየት ወደ ሀዋሳ ከተማ ተጉዞ የነበረ ሲሆን የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን እንዲጎበኝ  ተደርጓል  ።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮ- ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በመገምገም፥ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ለመተግበር መስማማቷን ተከትሎ  ነው  የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን የላከው ።

በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ኦስማን ሳለህ የሚመራው እና የፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብ ያካተተው ልኡክ ባሳለፍነው ማክሰኞ አዲስ  አበባ  በመግባት  በዛሬው  ዕለት ተልዕኮውን አጠናቆ ተመልሷል ።