ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩት የሰላም እንቅስቃሴ ለቀጠናው ሰላም መሠረት የሚጥል ነው -አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ለማስፈን የጀመሩት እንቅስቃሴ በቀጠናው በጎ የሆነ ተጽዕኖ የሚፈጥር መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።

 

የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ያደረገው ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማሻሻል የተወሰደ የመጀመሪያ የተግባር እርምጃ መሆኑንም ዋና ጸሐፊው አንስተዋል።

 

ሀገራቱ ለረጅም ጊዜ የነበረውን አለመግባባትና ውጥረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የጀመሩት ጥረት በቀጠናው ከፍተኛ የሆነ በጎ ተጽእኖ እንደሚኖረው መግለጻቸውን የዋና ጸሀፊው ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ዱጃሪክ አመልክተዋል።

 

ተመድ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የድንበር ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን፣ የሰላም ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆንና በሌሎች ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ጠቁመዋል።