የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲና መከላከያ ሚኒስቴር በጋራ በሚሰሩበት ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አደረጉ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና የኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስቴር መረጃ ዋና መምሪያ ተደምረው በሚሰሩበት ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

ሁለቱ መስሪያ ቤቶች አብረው የሚሰሩበትን ሁኔታ አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴር የመረጃ መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ሐሰን ኢብራሂም የሃገሪቷን መረጃ ማሰባሰቢያ መተንተኛ እና ማሰራጫ መንገዶችን ዘመናዊ በማድረግ በኩል በየጊዜው እያደገ የሚሄድ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ኤጀንሲው በአዋጅ ተሰጠውን ተግባር እና ሃላፊነት መሰረት አድርጎ ከመከላከያ ሚኒስቴሩ ስር ካሉ ልዩ ልዩ ተቋማት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተደምሮ ይሰራል ብለዋል፡፡

በፕሮጀክት አስተዳደር ስርአት እና የፕሮጀክት አፈፃፀም አስመልከቶ በሚፈለገው ደረጃ ግንኙነት ያለመደረጉ የፈጠረውን ክፍተት በመቅረፍ እና በመግባባት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ የመረጃ መሰብሰቢያ፣ መተንተኛ እና ማሰራጫ ስርዓቶችን በማዘመን ረገድ በጋራ ለመስራት ከመግባባት ላይ ደርሰዋል። (ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ)