መንግስት የሚያከናውናቸውን የለውጥ ተግባራት ለማደናቀፍ የሚጥሩ የጥፋት ሃይሎችን ማጋለጥ ይገባል

መንግስት እያከናወናቸው ያሉትን የለውጥ ተግባራት ለማደናቀፍ የሚጥሩ የጥፋት ሃይሎችን በማጋለጥ ህብረተሰቡ እንዲተባበር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ለኢዜአ በላከው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ እንዳስታወቀው፤ መንግስት በመላ አገሪቱ በህዝቡ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ እርምጃዎችን በቅደም ተከተል በመውሰድ ላይ ይገኛል።

በዚህም በርካታ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ከእስር እንዲለቀቁ በማድረግ፣ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መልካም ግንኙነትን በመፍጠርና ከኤርትራ ጋር የነበረው “ሞት አልባ ጦርነትም” ለመቋጨትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

እየተካሄደ ያለውን አገራዊ የለውጥ ሂደት አቅጣጫ ለማስቀየር ጥረት የሚያደርጉ የጥፋት ሃይሎች መኖራቸውን በመግለጫው አካትቷል።

በቅርቡ መንግስት ላካሄዳቸው ለውጦች ድጋፉን ለመግለጽ ህብረተሰቡ በመስቀል አደባባይ ባካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ኢትዮጵያዊ ስነ-ምግባር በጎደለው መልኩ በህዝብ ላይ ቦምብ በመወርወር ለንጹሃን  ዜጎች ህይወት መጥፋትና አካል መጉደል ምክንያት መሆኑንም ለአብነት ጠቅሷል።

እነዚህ ሃይሎች ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ ቅሬታ እንዲያስነሳና የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጉዳት እንዲደርስና የሃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ፣ የስልክ ኔትዎርክ እንዲጠፋ፣ መሰረታዊ የሸቀጦች አቅርቦት ላይ የዋጋ ንረት እንዲከሰትና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራዎች እንዲደናቀፍ በማድረግ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ እንዲማረር ጥረት እያደረጉ ነው።

በመሆኑን ጉዳዩን በጥልቀት የሚመረምርና የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ መንግስት አቋቁሞ እየሰራ ሲሆን ማንኛውንም ዜጋ ለኮሚቴው  ተገቢውን መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጽህፈት ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።

ሙሉ የአቋም መግለጫው ከዚህ በታች እንደሚከተለው ቀርቧል።(ኢዜአ)

                      ሳምንታዊ የመንግስት የአቋም መግለጫ

የህዝብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ የተጀመረው ፈጣን  ለውጥ ተጨባጭ ስኬቶችን ማስመዝገብ በመቻሉ  አሁን ላይ  ለውጡን  ማንም ሊያቆመው በማይችለው ደረጃ ላይ ደርሷል። ባለፉት ጥቂት ወራት መንግስት አገራዊና  ከባቢያዊ  ሁኔታዎችን   ታሳቢ በማድረግ  እየወሰዳቸው  ባሉ  እርምጃዎች  ፈጣንና  ተጨባጭ  ውጤቶች  በመመዝገብ  ላይ ናቸው።  ይሁንና እየመጡ ያሉ  ፈጣን  ለውጦች  ከስጋት ላይ የጣሏቸው አንዳንድ አካላት የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ በርካታ እንቅፋቶችን እያስቀመጡልን የህዝብና መንግስትን የለውጥ አቅጣጫ ለማስቀየር ሳይታክቱ በመስራት ላይ   ናቸው።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ  ለ17 ቀናት ባካሄደው  ጥልቅ ግምገማ በኢትዮጵያ ለሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችና ችግሩ ለፈጠረው አገራዊ ቀውስ  የድርጅቱ  የበላይ አመራሮች  ሃላፊነቱን  ወስደው፣  ህዝብንም  በይፋ  ይቅርታ  ጠይቀው፣  የተሳሳቱ አካሄዶችን ለማስተካከል   መወሰናቸው   ይታወሳል።  ይህን ውሳኔ  ተከትሎ  መንግስትና ድርጅት  በአገራችን  የሚስተዋሉ የህዝብ ቅሬታዎችን  ለመቅረፍ   የሚያስችሉ  በርካታ  እርምጃዎችን  በቅደም ተከተል  በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።  በዚህም  በርካታ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ከእስር ተለቀዋል፣ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር  መልካም ግንኙነትን  መፍጠር  ተጀምሯል፣ በትጥቅ ትግል ላይ  የተሰማሩ ሃይሎችም ሰላማዊ የትግል መስመርን ተቀላቅለዋል፣ በውጭ አገር የነበሩ ሚዲያዎች   በተፈጠረው  ምቹ  ሁኔታ  ተጠቅመው  ወደ አገር ቤት መመለስ ጀምረዋል፣ የዳያስፖራውም  የፖለቲካ አተያይ መቀየር ጀምሯል፣  ከኤርትራ ጋር የነበረው  ሞት አልባ  ጦርነትም  መቋጫ በማግኘት ላይ ነው። ይሁንና  እየተካሄደ  ያለው  አገራዊ ለውጥ  ቀድሞ ለፈጸሙት በደልና ጥፋት ተጠያቂነትን ያስከትልብናል ወይም  ቀጣይ  ህገ ወጥ የሆነውን  የጥቅም  ማጋበሻ  መንገድ ይዘጋብናል  የሚል ስጋት የፈጠረባቸው አካላት እንዳሉ መገንዘብ ተችሏል።

በመሆኑም እነዚህ  ቡድኖች የህዝብን የለውጥ ፍላጎት ለማደናቀፍ እስከታችኛው እርከን በዘረጓቸው የጥፋት መረቦቻቸው  በመጠቀም  በረቀቀና ውስብስብ  በሆነ መንገድ  የለውጥ ሂደቱን አቅጣጫ  ለማስቀየር  ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ለአብነት  በቅርቡ እንኳን  መንግስት እስካሁን ላካሄዳቸው ለውጦች  ምስጋና ለማቅረብና በቀጣይም ድጋፉን ለማረጋገጥ  ህብረተሰቡ በመስቀል አደባባይ ባካሄደው  የድጋፍ ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያዊ  ስነ ምግባርነት በጎደለው መልኩ በህዝብ ላይ  ቦምብ  በመወርወር  ለንጹሃን  ዜጎቻችን ህይወት መጥፋትና አካል መጉደል ምክንያት ሆነዋል። እነዚህ  ሃይሎች በዚህ ብቻ  ሳይታቀቡ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የህዝብን ትክክለኛ ጥያቄዎች ከለላ በማድረግ አብረው ለዘመናት የኖሩ ህዝቦችን እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ በማድረግ ላይ ናቸው።  በዚህም  ሳቢያ  በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተከሰቱ ሁከቶች    ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድልና ንብረት እንዲወድም እያደረጉ  ናቸው።

ከዚህም ባሻገር  እነዚህ ሃይሎች  በህዝቡ ውስጥ ባደራጇቸው  የጥቅም ተጋሪዎቻችው ሳቢያ  ህብረተሰቡ  በመንግስት  ላይ  ቅሬታ  እንዲያስነሳና  የለውጥ ሂደቱን አቅጣጫ ለማስቀየር በአገልግሎት  ሰጪ  ተቋማት  ላይ ጉዳት እንዲደርስና  የሃይል  አቅርቦት እንዲቋረጥ፣   የስልክ  ኔትዎርክ እንዲጠፋ፣  መሰረታዊ  የሸቀጦች አቅርቦት ላይ ጫና በመፍጠር  የዋጋ ንረት  እንዲከሰት  እንዲሁም  የተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት  ስራዎች እንዲደናቀፉ  በማድረግ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ  እንዲማረርና  የተጀመረው  የለውጥ  ፍላጎት  አቅጣጫውን ስቶ  እንዲንገራገጭ በመፈራገጥ ላይ ናቸው።

ይህን ጉዳይ በጥልቀት የሚመረምርና የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርብ  ኮሚቴ መንግስት አቋቁሞ  እየሰራ  በመሆኑ ማንኛውንም ዜጋ ለኮሚቴው  ተገቢውን መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪውን እያቀረበ፤ የተጀመረው  የህዝብና የመንግስት የለውጥ ጉዞ  ማንም  ሊያስቆመው  እንደማይችል በግልጽ ሊታወቅ  ይገባል። በእንዲህ ያለ የወረደና ርካሽ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ ቡድኖችም ይሁኑ ግለሰቦች ከህዝብ ዕይታ የተሰወሩ ባለመሆናቸው  ህብረተሰቡ  ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ  የአካባቢውን ጸጥታ  በንቃት ከመጠበቅ ባሻገር ማንኛውንም አጠራጣሪ ጉዳይ በገጠመው  ጊዜ  ሁሉ  ለአካባቢው የጸጥታ ሃይል  በፍጥነት  ማሳወቅ ይኖርበታል።