ዓለም አቀፍ በረራዎችን ለማደናቀፍ የሞከሩና ያስተባበሩ ባለሙያዎች ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አዋለ

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዓለም አቀፍ በረራዎችን ለማደናቀፍ የሞከሩና የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎችን የስራ ማቆም አድማን ሲያስተባብሩ እና ሲመሩ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ 9 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ተኮላ አይፎክሩ እንዳስታወቁት፥ ግለሰቦቹ የበረራ ሂደቱን ለማስተጓጎል በተለይም ከውጭ ሀገራት የሚመጡ አውሮፕላኖች እንዳያርፉ ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

እንዲሁም በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሰራተኞች ዘንድ ሲደረግ የቆየውን የስራ ማቆም አድማ አስተባብረዋል እንዲሁም መርተዋል ተብለው ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ተኮላ፥ ግለሰቦቹ በፍርድ ቤት መያዣ ወጥቶባቸው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል ብለዋል።

ሠራተኞቹ ባለፉት ጊዜያት ከደመዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋር ተያይዞ የመብት ጥያቄ አቅርበው ዋልታ ቴሌቪዥንም በተከታታይ መዘገቡ ይታወሳል፡፡