ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት የለጋሽ አካላትና የህብረተሰቡ ድጋፍ ተጠየቀ

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት የለጋሽ አካላትና የህብረተሰቡ ድጋፍ ተጠየቀ።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት ለጋሽ አካላትና ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ኮሚሽኑ ተፈናቃዮቹ ከሚገኙበት የኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በቅንጅት ለመስራት የባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው መላኩንም ገልጿል።

ሰሞኑን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 91 ሺህ 348 መድረሱንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ ግጭቱ ሲፈጠር ከክልሉ ተፈናቅለው ወደ ምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ የተሰደዱት ተጎጂዎች ቁጥር 36 ሺህ 291 ነበር።

በአካባቢው ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ሌሎች 55 ሺህ 57 ሰዎች ከቀያቸው በመፈናቀል በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

አሁን ላይም የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለተጎጂዎች መላኩንም ገልጸዋል።

በኮሚሽኑ በኩል የአልባሳት፣ የቤት ቁሳቁስ፣ አልሚ ምግብና የጊዜያዊ መጠለያ ድጋፍ ቢደረግም ከችግሩ ክብደት አኳያ እርዳታው በቂ አይደለም ነው ያሉት።

በመሆኑም ለጋሽ አካላትና ህብረተሰቡ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ ለሚገኙ ዜጎች የተለመደ ድጋፉን እንዲያደርግ የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጠይቋል።

በአሁኑ ወቅት በመላ ሃገሪቱ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት፥ ከ8 ሚሊየን በላይ ዜጎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን እነርሱን ለመደገፍ ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል ተብሏል።