ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በዓለም አቀፍ በቀጣናዊና በሦስትዮሽ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ሞቃዲሾ ገቡ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከኤርትራው አቻቸው ኦስማን ሳልህ ጋር በዓለም አቀፍ፣ ቀጣናዊና በሦስትዮሽ ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማካሄድ በትላንትናው ዕለት ሶማሊያ ገብተዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች ሞቃዲሾ አደን አዴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሶማሊያ አቻቸው አህመድ ኢሴ አዋድ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ዶክተር ወርቅነህ ከኤርትራ አቻቸው ጋር በሞቃዲሾ ከሶማሊያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በዓለም አቀፍ፣ በቀጣናዊና በሦስትዮሽ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያካሂዳሉ።

በምስራቅ አፍሪካ የተገኘውን አበረታች ሰላም በማጎልበትና የኢኮኖሚ ትብብርን በማሳለጥ ቀጣናዊ ውህድትን ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ያካሂዳሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሶማሊያና ከኤርትራ አቻዎቻቸው ጋር ከዚህ በፊት በአስመራ መገናኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ወደ ጂቡቲ በማቅናትም በአካባቢያዊ የሰላምና መረጋጋት ጉዳዮች ላይ መምከራቸው አይዘነጋም። (ኢዜአ)