በደርግ ዘመነ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ሃገራቸው ገቡ

በደርግ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትና ትምህርት ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በዛሬው እለት ወደ አገራቸው ገቡ። 

ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ሲደርሱ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ነብያት ጌታቸውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የቀድሞው ሚኒስትር በቦሌ አለም ዓቀፍ አየር መንገድ በሰጡት መግለጫ የደርግን አገዛዝ በመቃወም ሃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው በመልቀቅ ላለፉት 32 አመታት ኑሯቸውን በአሜሪካ አድርገው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ያለውን አጠቃላይ የለውጥ ሂደት ለመመልከት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅና የተጀመረውን የሰላም፣ የፍቅርና የመደመር ሂደት በሚችሉት መጠን ለመደገፍ ወደ ሃገራቸው መምጣታቸውንም አንስተዋል።

ፖለቲካዊ ውድድር የማድረግም ሆነ ስልጣን የማግኘት ፍላጎት የለኝም ያሉት ኮሎኔል ጎሹ፥ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ የተጀመረውን የሰላም፣ እርቅና የመደመር እንቅስቃሴ ሁሉም ሊደግፈው እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ይህን የእርቅና የመደመር ጉዞ ላስጀመሩት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ወጣቱም የሰላምን አስፈላጊነት በሚገባ ተገንዝቦ ለግጭት ከሚዳርጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብም ጠይቀዋል።

በሃገሪቱ አሁን ላይ ማንኛውንም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ መፍትሄ ማግኘት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ለዚህም ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ ለማጋራትና ለሰላማዊ ሂደቱ መጎልበት የተቻላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ  ተናግረዋል ።( ምንጭ: ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት)