መከላከያ ሠራዊትን በሁሉም መስክ ብቁ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ይቀጥላል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

መከላከያ ሠራዊትን በሁሉም መስክ ብቁ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት በከፍተኛ ግለት እንደሚቀጥል የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት   ከክፍለ ጦር አዛዦች በላይ ያሉ  የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች  ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊት በአንዲት አገር የሚኖር ብቸኛው የታጠቀ አካል መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ኃላፊነት በህገ-መንግሥታዊ መልኩ መወጣት ይገባልም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት የመከላከያ ልህቀትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የአመራር ክህሎቶች የግዳጅ አፈፃፀም ሂደት ላይ ኃይልና ሥልጣንን በተገቢው መጠን፣ አግባብና ሁኔታ በመጠቀም ቅቡልነት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 87/4 መሠረት “መከላከያ በማናቸውም ጊዜ ለህገ መንግሥቱ ተገዥ ይሆናል” በሚል በተለየ አፅንኦት መከላከያን ከህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ጠባቂነትና ተገዥነት ጋር አቆራኝቶታል፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሃገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ላይ የምታፈሰው በጀትና የምትሰጠው ትኩረትም ይህን ቃል ኪዳን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በህገ መንግሥት በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ለግዳጅ ሲሰማራ በታጠቀው መሳሪያ ምክንያት ኃይል ቢኖረውም እርምጃው ቅቡልነትን በሚያረጋግጥ መልኩ በከፍተኛ ጥንቃቄ ፣ የህግ ተገዥነት ለህዝብ ተቆርቋሪነት ስሜት ማከናወን እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

ይህን ለማረጋገጥ ያሉ የግዳጅ አፈፃፀም መመሪያዎች እንደሚከለሱና በግዳጅ አፈፃፀም መመሪያው መሠረት ጥብቅ የእዝና ቁጥጥር ስርዓት በማስፈን መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

መከላከያ ኃይል አለኝ ብሎ እርምጃ የማይወስድ ቢሆንም ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ ግን በተሰጠው ሥልጣን ልክ በጥብቅ የግዳጅ አፈፃፀም መመሪያ የተቃኘ ፣ ሠላም ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ይሁንታ የሚሰጡት ተግባራዊ መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሰባት ወራት መከላከያ በከፍተኛ የለውጥ ጎዳና ላይ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጡም በህጋዊ ማዕቀፎች ፣ በአደረጃጀት፣ በመፈፀም ብቃትና በትጥቅ የሚገለፅ ነው።

በህጋዊ ማዕቀፍ ረገድ የመከላከያ ሠራዊት መቋቋሚያ አዋጅ የባህር ኃይል አደረጃጀትን አካቶ እንዲሁም ወደፊት የሳይበርና የህዋ /ስፔስ ምህዳሮችን ለማካተት በሚያስችል መልኩ ተሻሽሏልም ብለዋል፡፡

ዘመናዊው አውደ ውጊያ በሚጠይቃቸው አምስቱም ምህዳሮች፣/ምድር አየር/፣ ባህር፣ ሳይቨር እና ህዋ/ ዝግጁ የሆነ መከላከያ ሠራዊት የመገንባት ሂደት መጀመሩም ተገልጿል።

የአሠራር መመሪያዎች እንዲዳብሩና ዘመናዊ ሠራዊት ሊኖረው በሚገባው ደረጃ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓልም ተብሏል ፡፡

የሃገሩቱ አቅም በፈቀደ መጠን ቴክኖሎጂን የሚታጠቅ፣ በራሱ አቅም መጠን፣ ማሳደግ ብሎም መፍጠር የሚችል እንዲሆን በርካታ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን መከላከያ ከቴክኖሎጂ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለውና እንደ ሌሎች  አገራት ከራሱም አልፎ ለሌሎች ዘርፎች ምንጭ መሆን የሚችል የቴክኖሎጂ ማዕከል እንዲሆን እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

መከላከያ ሠራዊቱ  በሁሉም ደረጃዎች በህገ መንግሥቱ እንደተቀመጠው የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ተዋፅኦ የጠበቀ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገፅም በመግለጫው ተጠቅሷል። 

ከዚህ ቀደም የነበረው አደረጃጀት በርካታ ማነቆዎች የነበሩት፣ የሲቪል መከላከያ ቅንብርና በሚገባው ደረጃ ያላካተተ በመሆኑ ሰፊ ጥናት ተደርጎ አዲስ አደረጃጀት ፀድቋል ነው የተባለው፡፡

የፋይናንስ አጠቃቀምና አወጣጥ ስርዓት ዘርፉ የሚጠብቀው ሚስጥራዊነት እንደተጠበቀ  ሆኖ በግልጽ መመሪያዎች እንዲመራ የሚያስችል አሰራር  መዘርጋቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ መከላከያ በዘመናዊ ትጥቅ እንዲደራጅና ግዳጅ የመፈፀም ብቃቱ ከፍተኛ እንዲሆን የሚያስችሉ የተጠኑ ሥራዎች እየተከናወነ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ገልፀዋል። (ምንጭ፡-ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት)