የኢፌዴሪ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየፈጸመ ያለውን ተግባር የአማራ ክልል መንግስት ይደግፋል

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እያከናወነ ለሚገኘው ተግባር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ያለውን ድጋፍ  ገልጿል ።

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ፥ ለህግ የበላይነት ለማስከበር  ሁሉም ዜጋ  የሚገባውን ሊወጣ እንደሚገባም አስታውቋል።

መንግስት በሰከነ መንገድ መረጃዎችን በማሰባሰብና በማስረጃ በመደገፍ በሀገሪቱ ላይ ሲደርስ የነበረውን የሌብነት ተግባር ለማስቆም የሄደበት በሳልነት የተሞላበት አመርቂ መንገድን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንደሚያደንቅ ገልጿል።

በዜጐች ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦች ለህግ እንዲቀርቡ የተወሰደውን እርምጃ የክልሉ መንግስት እንደሚደግፍ ያስታወቀ ሲሆን፥ በተጨማሪም የሚጠበቅበትን ማንኛውንም ህጋዊ ተግባር ለመፈፀም ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

ሌብነትና ኢ-ሠብአዊ ድርጊት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች የትኛውንም ብሄር አይወኩሉም ያለው መግለጫው፥ እነዚህ አካላት ውክልናቸው ለራሳቸው እና ለጥቅም አጋሮቻቸው ብቻ የሚውል  መሆኑን ተናግረዋል ።

በመሆኑም የህዝብ ሀብት ከድሃ ጉሮሮ የነጠቁ ግለሰቦች በህግ ጥላ ሥር የመዋላቸው ምክንያት ሌብነትና ኢ-ሰብአዊነት የጎዳው ተግባራቸው እንጂ የትኛውም ህዝብ መገለጫ ሆኖ ሊወሠድ እንደማይገባም አስታውቋል።

የኢፌዴሪ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እያከናወነ ባለው ተግባር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ያለውን ድጋፍ እንደሚገልጽም  አመልክቷል።

በተጨማሪም ትግሉ ውጤታማ እንዲሆን ህገ መንግስታዊ ግዴታቸውንና የህዝብ አደራ በትጋት የተወጡ አካላት በተለይም የፀጥታው መዋቅር እያደረገ ያለውን ጥረት የክልሉ መንግስትና ህዝብ እንደሚያደንቅም በመግለጫው ተገልጿል።

በቀጣይም የህግ የበላይነት እና ፍትህን ለማስከበር በሚደረገውን ማንኛውም እንቅስቃሴ ዳር ለማድረስ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ በቁርጠኝነት እንደሚሠለፍም መግለጫው አረጋግጧል።