በጋምቤላ ለታዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች የአመራሩ ችግር መሆኑ ተገለጸ

በጋምቤላ ክልል ለታዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች በየደረጃው የሚገኙ የጋህአዴን አመራር አካላት ችግር መሆኑ ተገለጸ፡፡

ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የድርጅቱ የአመራር አካላት በጋምቤላ ከተማ እያካሄዱት ያለው ጥልቅ ግምገማ እንደቀጠለ ነው።

በዚሁ የግምገማ መድረክ የድርጅቱ አመራሮች እንዳሉት በክልሉ ለታዩት  ክፍተቶች ሙስና፣ ብልሹ አሰራርና የአመራሩ የማስፈጸም አቅም መዳካም የፈጠሯቸው ችግሮች ናቸው።

ከአመራሮቹ መካከል አቶ ኡኩኝ ኦኬሎ  በክልሉ የተደረጀ ሌብነትና የብለሹ አሰራር ችግሮች ለህዝቡ ሊሰሩ ቃል የተገቡ የልማት ፕሮጀክቶች በጅምር እንዲቀሩ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል ።

ከክልል እስከ ወረዳ በሚገኙ መዋቅሮች አመራሩ የህዝብን ጥቅም ወደ ጎን በመተው ቤተሰቡንና ዘመድ አዝማዱን ከመንግስት ደንብና መመሪያ ውጪ በመቅጠር የህዝብና የመንግስትን ሀብት ለግል ጥቅሙ ሲያውል እንደነበርም ገልጸዋል።

በክልሉ የሚካሄዱ ምደባዎችና ሹመቶች ብቃትን ሳይሆን ጎሳን፣ ዘመድንና ጓደኝነት መሰረት ባደረጉ መልኩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌለው ተሳታፊ አመራር አቶ ጁል ኛንጋል ናቸው።

በክልሉ ለሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶች በሚዘጋጁ የስራ እድሎች አመራሩ ቤተሰቡን አደረጅቶ ስልሚያስገባ  ወጣቱ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱንም አመልክተዋል።

ሌላው ተሳታፊ አቶ ማበር ኮር በበኩላቸው ” በተለይም የውስጥ ድርጅታዊ ዴሞከራሲዊ ትግል እየተዳከመ በመምጣት አመራሩ የህዝብ ስልጣን ለግል ጥቀሙ ሲያውል ነበር”  ብለዋል።

በዚህም ምክንያት አመራሩ በነበረው የተበላሸና የተዘባ አመለከካት የማስፈጸም አቅሙ እየመከነ ከመምጣቱም በላይ የህዝብን ችግር ለመፍታት የሚሰራ አመራር መጥፋቱንም  ተናግረዋል።

በክልሉ ለተፈጠሩት የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አመራሩ ኃላፊነት ሊወስድ እንደሚገባም ተናገሪዎቹ አመልክተዋል።

የድርጀቱ ሊቀመንበር አቶ ኡጁሉ ኡሞድ ” በተለይም ከክልሉ እስክ ወረዳ አመራር ስር ሰዶ ያለው የሙስና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የማስወገዱና የህዝብን ስልጣን ለህዝብ ጥቅም የማዋሉ ተግባር ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ነው “ብለዋል።

በተለይም የቡደንተኝነት፣ የጎሰኝነትና ብሄረተኝነት አሰተሳሰብ ችግሮች ከአሁን በፊት ለተከሰቱት ችግሮች ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ጠቁመው እነዚህን አስተሳሰቦች ለማምከንም የድርጀቱ አመራሮችና አባላት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከክልል አስከ ወረዳ የሚገኙ ከ550 በላይ የድርጅቱ አመራር አካላት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እያካሄዱት ያለው ጥልቅ ግምገማ እንደቀጠለ ነው።