የጃፓኑ የሳይበር ደህንነት ሚኒስቴር በዘመናቸው ኮምፒውተር ተጠቅመው አለማወቃቸው አስገራሚ ሆኗል

የጃፓኑ የሳይበር ደህንነት ሚኒስቴር ዮሺታካ ሳካሩዳ  በዘመናቸው ኮምፒውተር ተጠቅመው እንደማያውቁ ማመናቸው በበርካቶች ዘንድ ግርምትን አጭሯል፡፡

ቴክኖሎጂ እንደ ጉድ በሚፈበረክባት ሀገረ ጃፓን በህይወቴ ኮምፒውተር ነክቼ አላዉቅም የሚል ሰዉ ቢገጥምዎ ምን ይሉ ይሆን?

በጃፓን በቅርቡ የመረጃ ደህንነት ሚኒስትር ሆነዉ የተሾሙት የ68 አመቱ ዮሺታካ ሳኩራዳ ከወጣትነት ዘመናቸዉ ጀምሮ በሀገሪቱ ባሉ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች በሀላፊነት አገልግለዋል፡፡

ታዲያ እኚህ ሰዉ አስካሁን ድረስ ምንም አይነት ኮምፒዉተር ተጠቅመዉ  እና በጭራሽም ኮምፒዉተር ነካክተዉ እንደማያዉቁ ለጃፓን የታችኛዉ ምክር ቤት ገልፀዋል፡፡

ጎልማሳው ዮሺታካ ኮምዩተር ተጠቅመው እንደማያውቁ ያመኑት የሀገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት ካቢኔ ለጥያቄ ባስጠራቸው ወቅት ነውም  ተብሏል፡፡ ካቢኔዉ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳላቸዉ ሲሆን ለአንዱም እንኳን አጥጋቢ መላሽ አልሰጡም ነው የተባለው፡፡

በሀላፊነት ባገለገሉባቸዉ ወቅቶች ሁሉ በኮምፒዉተር የሚሰሩትን ስራዎች በፀሀፊያቸዉ እና በሌሎች ሰራተኞቻቸዉ እንደሚከወኑም ተናግረዋል፡፡ እሳቸዉ በኮምፒዉተር የሚሰሩ ስራዎችን አይስሩ እንጂ እያንዳዱ ሰራ እንዳይስተጓጎል ጥሩ አመራር እንደሚሰጡ ነው ለምክርቤቱ ካቢኔ የገለፁት፡፡

ሰዉዬዉ የሰጡትን ምላሽ ተከትሎ የማህበራዊው ሚዲያ መነጋገሪያ ሆነው የሰነበቱ  ሲሆን በርካታ ሰዎች እና ፖለቲከኞች እያፌዙባቸዉ እንደሚገኙ  ዘገባዉ አስታዉቋል፡፡

በሌላ በኩልም የሰዉየዉ ዋነኛ ተፎካካሪዎች አንዳችም ስለኮምፒዉተር አጠቃቀም  በቂ ግንዛቤ  የሌለዉ ሰዉ የመረጃ ደህንት ሀላፊ አድርጎ መሾም የማይታመንና አስገራሚ ድርጊት ነዉ ብለዋል፡፡

አንዳንዶች ደግሞ በተቃራኒዉ ምናልባትም ኮምፕዩተር ያለመጠቀማቸው ሚስጥር በመረጃ በርባሪዎች እጅ እንዳይወድቁ በማሰብ እና ለዛ እንዲረዳቸዉ ነዉ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡

ዮሺታካ ለረጅም ዓመታት የጃፓን የፓርላማ አባል ሆነው እንዳገለገሉ የተገለጸ ሲሆን፥ የመረጃ መረብ ደህንነት ሚኒስትር በመሆን የተሾሙት ባለፈው ወር እንደነበር አስታውሶ የዘገበው ዘቴሌግራፍ ነዉ፡፡