ምክር ቤቱ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ ሾመ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን  የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ  በማድረግ  በአብላጫ ድምጽ ሾሟል ።

የቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር፣ዳኛና ጠበቃ የነበሩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የኢፌዴሪ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  በማድረግ  በአብላጫ  ድምጽ  አፅድቋል  ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለብሔራዊ  ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት እጩ እንዲሆኑ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ  በዳኝነት ፣ በሰብዓዊ መብት ተከራካሪነትና  ለህግ ጥብቅና በመቆም ያካበቱት ልምድ ለእጩነት እንዳበቃቸው ተናግረዋል ።

ወይዘሪት ብርቱካን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በህግ ፊት እኩል አይን መታየት አለበት ፤ ህግም ሁሉንም የሚያስተዳድርና የሚገዛ መሆን አለበት  በሚል ጽኑ  አቋም ያላቸውንና ፍርድ ቤት በነበሩበት ወቅት በማንም ያልተደለሉ ቆራጥ ሰው  መሆናቸውን በተግባር እንዳሳዩ  ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ  ለምክር ቤቱ ተናግረዋል ።

ከዚህ ቀደም ወይዘሪት ብርቱካን በአሁኑ ወቅት ናሽናል ኢንዳውመንት ፎር  ዴሞክራሲ በተባለ ተቋም  ላይ  እየሠሩ ሲሆን  በኢትዮጵያ ምርጫ  ከዚህ  ቀደም የተሳተፉና  በፓርቲ አመራርነት  ልምድ  እንዳላቸውና በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲና አመራርነት የወጡ መሆናቸውን  ለምክር ቤቱ ተገልጿል ።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ  ተቋማት ውስጥ ግለሰቦች ሳይሆኑ ተቋማት እንዲገነቡ ለማስቻል  የህግ ልዕልናን  የሚያቁ ሰዎች  በመሪነት እንዲቀመጡ ለማድረግ  በማሰብ ወይዘሪት ብርቱካንን በእጩነት ያቀረቡ መሆኑን  ጠቅላይ ሚንስትሩ  ለምክር ቤቱ አስረድተዋል ።

እንደዚህ አይነት ውሳኔም የኢትዮጵያ መንግሥት ዴሞክራሲን  ለማረጋገጥ  ቁርጠኝነት  ላይ መድረሱን  የሚያሳይበት  እንደሆነም በርካቶች ምስክርነት እየሠጡበት ስለመሆኑ  ተገልጿል ።

ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት በእጩነት ለቀረቡት ወይዘሪት ብርቱካን  ድምጽ  ከመሠጠቱ   በፊት  የምክር ቤቱ አባላት   ምን ያህል  ወይዘሪት ብርቱካን ቀደም ሲል የተቃዋሚ የፖለቲካ  አመራርና አባል ስለነበሩ  ምንያህል  በነጻነትና  በገለልተኛነት ሊያገለግሉ ይችላሉ  የሚል  ጥያቄ  አንስተው በጠቅለይ ሚንስትሩ ምላሽ ተሠጥቷል  ።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ  ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ  የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ሰብሳቢ እንዲሆኑ ድምጽ የሠጠ ሲሆን  በአራት ተቃውሞ ፣ በሶስት ድምጸ ተዓቅቦና  በአብላጫ ድምጽ ድጋፍን   በማግኘት  የምርጫ  ቦርድ  ሰብሳቢ ሆነው  ተሾመዋል ።