ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ

ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በምዕራብ ጎንደር ዞን የቋራ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ኢንስፔክተር አንለይ መልካሙ እንደገለፁት ከሱዳን ወደ ቋራ ወረዳ ሲገባ የነበረ አምስት ብሬንና ሁለት ሺህ 737 ጥይት በቁጥጥር ስር ውሏል።

መሳሪያው ትላንት ከቀኑ 5:00 ሰዓት አካባቢ በግል የንግድ ተሽከርካሪ ተደብቆ ለማለፍ ሲሞክር በወረዳው ልዩ ስሙ ነብስ ገበያ ቀበሌ ቁጥር አንድ በተባለ ቦታ መያዙን ተናግረዋል።

መሣሪያውን ለማስገባት የሞከሩ የላንድ ክሩዘር አሽከርካሪና ሌላ አንድ ተባባሪ ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ላይ መሆናቸውን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል። 

መሣሪያው በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋሉን የገለፁት ኢንስፔክተሩ ህብረተሰቡ ወደ ፊትም ተሳትፎን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። (ኢዜአ)