የወባን በሽታ ከአገሪቱ ጨርሶ ለማስወገድ በአጎበር አጠቃቀም ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ

የወባን በሽታ ከአገሪቱ ጨርሶ ለማስወገድ በአጎበር አጠቃቀም ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በሽታውን ለማስወገድ የሚከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በአጎበር አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ግድፈቶችን ለማስወገድ ለህብረተሰቡ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ሊዘረጉ እንደሚገባ ነው የተገለጸው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በአውሮፓውያኑ 2030 ወባን ጨርሶ ለማጥፋት የተያዘውን ፕሮግራም ለመተግበር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ለመገምገም የሚያስችል ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የትግራይ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የኦሮሚያ፣ የሀረሪ ክልሎችና የድሬደዋ አስተዳደር በየክልላቸው ወባን ጨርሶ ለማስወገድ ባለፉት አመታት ያከናወኗቸውን ተግባራት ለተወያዮቹ አቅርበው ለቀጣይ ስራ የሚያግዙ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰጥቶባቸዋል።

በዋናነትም በአንዳንድ አካባቢዎች ከተግባሩ ውጪ ለግብርና ምርቶች መሰብሰቢያ፣ ለቆሻሻ ማጠራቀሚያነት፣ ለአጥርና መፀዳጃ ቤቶች መከለያ እና ለመሳሰሉት እየዋለ ያለው የወባ መከላከያ አጎበር ለተገቢው አገልግሎት እንዲውል የማስተማሩ እና የመከታተሉ ስራ መጠናከር እንዳለበት በአፅንኦት ተወያይተዋል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት የወባ መከላከልና ማጥፋት ኬዝቲም አስተባባሪ አቶ መብራሃቶም ኃይለ ውይይቱ ወባን ጨርሶ ለማስወገድ የተያዘውን ዕቅድ በመተግበር ረገድ በቀዳሚነት የተቀመጡ ግቦችን አፈፃፀም ለመፈተሽና ለቀጣይ ስራዎች የሚያግዙ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የወባ ትንኝ መራባትን የመቆጣጠር ስራ፣ የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት፣ የአጎበር ስርጭት፣ የህክምና አገልግሎት አቅርቦትን የማጠናከርና የመሳሰሉት ስራዎች በመከናወናቸው በወባ የሚጠቁና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን ተናግረዋል።

ላለፉት 15 ዓመታት የወባ ወረርሽኝ ስለመከሰቱ ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሪፖርት አለመደረጉን የተናገሩት አቶ መብራሃቶም በየጊዜው የተመዘገበውን የወባ ወረርሽኝ መቀነስ አዝማሚያ የተረዳው የዓለም ጤና ደርጅትም ለኢትዮጵያ ዕውቅናና ሽልማት ማበርከቱን አስታውሰዋል።

ሰሞኑን የአለም ጤና ድርጅት ባሰራጨው ሪፖርትም በኢትዮጵያ ከአውሮፓዊያኑ 2016 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት 40 በመቶ የወባ ስርጭትን ለመቀነስ የተያዘውን ዕቅድ ሀገሪቱ በ2018 35 በመቶ ላይ መድረሷን ጠቅሶ አስፍሯል።

ከስድስትና ሰባት ዓመታት በፊት በዓመት እስከ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች በወባ እንደሚያዙ ሪፖርት ይደረግ ነበር ያሉት አስተባባሪው አምና በተደረገ ሪፖርት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች በወባ መያዛቸው ረፖርት መቅረቡ ለውጥ እንዳለ ያሳያል ብለዋል።

በዓለም ደረጃ በተለይ በአፍሪካ የወባ ወረርሽኝ እየጨመረ ስለመምጣቱ ሪፖርት እንደደረሰው የአለም ጤና ድርጅት የገለፀ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ፓኪስታን፣ ሩዋንዳ እና ህንድ የወባ ወረርሽኝ የቀነሰባቸው ሀገሮች ሆነው ተመዝግበዋል።

ወባን ጨርሶ የማስወገድ ስራን ለመገምገም የተከፈተው መድረክ እስከ መጪው ዕሮብ ይቀጥላል። (ምንጭ፡- የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር)