አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከየመን ማውጣቱን ገለፀ

አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በየመን የነበሩ 102 ኢትዮጵያውያን ስተደተኞችን በሰንዓ  በኩል ማስወጣት መቻሉን አስታወቀ።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በመያዝ ከየመን ሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳው አውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ የቀጥታ በረራ እንደሚያደርግ በሀገሪቱ የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት ሳባ አል ሙአላሚ ገልፀዋል።

በሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል በፍቃደኝነት ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ተግባር ሲከናወን ከፈረንጆቹ 2015 በኋላ ይህ  የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

ከዚህ ባለፈ በቀጣይ ቀናት 402 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የያዙ አውሮፕላኖች ከየመን ሰንዓ በመነሳት ወደ አዲስ አበባ እንደሚበሩ ተጠቁሟል።

አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በየመን የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ስደተኞችን በፍቃደኝነት በሆዴአዲያ ወደብ በኩል ወደ ሀገራቸው ሲመልስ እንደቆየ መረጃዎች ያመላክታሉ።/አናዱሉ/