በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

በሙስናና ሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩት ግለሰቦች ለ2ኛ  ጊዜ  በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት  ቀረቡ ።

በእነ ጎሃ አጽብሃ መዝገብ በሰብዓዊ መብት ጥሰት 36 እና በእነ ብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርዲ መዝገብ በሙስና ወንጀል 28 በአጠቃላይ ከ60 በላይ ተጠርጣሪዎች፥ ለ2ኛ ጊዜ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

በሙስና የተጠረጠሩት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሰራተኞች እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኝ ሲሆን፥ከተጠርጣሪዎቹ መካከል እነ ብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርዲ፣ ብርጋዴር ጄኔራል በረኸ በየነ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ጥጋቡ ፈትለአብ እና ብርጋዴር ጄኔራል ሀድጉ ገብረጊዮርጊስ ይገኙበታል።

የፌዴራል መርማሪ ፖሊስም ተጠርጣሪዎቹ ከደህንነት ቢሮ፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላቸው የስራ ሃላፊነትና ሚና በሽብር የተፈረጁ ግለሰቦችን በማፈን፣ ስውር እስር ቤት አስገብቶ ኢሰብዓዊ የሆነ ድርጊት እንዲፈጸምባቸው ያደረጉ መሆናቸውንና በተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተሳትፈዋል በማለት ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ካደመጠ በኋላ ከቀረቡት 36 ተጠርጣሪዎች ውስጥ ሁለቱን በዋስ እንዲወጡ እንዲሁም 16ቱ ተጠርጣሪዎች ደግሞ መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው በማለት ፈቅዷል፡፡