የኦስትሪያ መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ከርዝ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

የኦስትሪያው መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ከርዝ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ መግባታቸው ተገለጸ ።

የኦስትሪያው መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ከርዝ ዛሬ ጥዋት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ከርዝ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ከርዝ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በጀርመን በርሊን በተካሄደው የቡድን 20 ሀገራት ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተገናኝተው ነበር።

በተገናኙበት ወቅትም የሁለትዮሽ ስብሰባ ያደረጉ ሲሆን፥ ሀገራቱ የጋራ ግንኙነታቸውን ለማጠንከር በትብብር እንደሚሰሩ መስማማታቸው ይታወሳል።