በአዲስ አበባ ከተማ ቅዳሜ እና እሁድ ይካሄዳል የተባለው ሰላማዊ ሰልፍ ዕውቅና የለውም -የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

አንዳንድ ግለሰቦች ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን የገለጸው ፖሊስ ሰልፉ በከተማ አስተዳድሩም ሆነ በፖሊስ ኮሚሽኑ እውቅና የሌለው መሆኑን አስታዉቋል።

በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮች ሊቀረፉ ይገባል፣ እንዲሁም የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደግፋለን የሚሉ ሓሳቦችን ምክንያት በማድረግ ሊካሄድ የታሰበው ሰልፍ ምንም ዓይነት እውቅና የሌለው መሆኑን የኮሚሽኑ ኢንዶክተሪኔሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ህገ መንግስታዊ መብት ቢሆንም በተጠቀሱት ቀናት ሰልፍ እናደርጋለን የሚሉ አካላት የሰልፉን መነሻ እና መድረሻ፣ የአስተባባሪዎቹን ማንነትና አድራሻ እንዲሁም መሰል ተያያዥ ጉዳዮች ለሚመለከተው አካል ባለማሳወቃቸው ምክንያት አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ እንደሚቸገር ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ይህንን መልዕክት ተላልፎ ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ የሚደረግ ከሆነ በህግ አግባብ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳስቧል፡፡