ምክር ቤቱ የመከላከያ ሠራዊትና የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባውም ሁለት ረቂቅ አዋጆችን አፅድቋል።

ምክር ቤቱ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሠራዊት አዋጅ ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ከተወያየበት በኋላ ነው በ1 ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ ያፀደቀው።

የመከላከያ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውስጥ ከ28 በላይ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ተደርጓል።

ከዚህ ውስጥም የመከላከያ ሰራዊት ከዚህ በፊት ከነበረው በተጨማሪ የባህር ሃይል እና እንደ አስፈላጊነቱ የስፔስና የሳይበር ሃይሎችን እንዲያቅፍ ተደርጎ ቀርቧል።

ከዚህ ባለፈም በመኮንኖች ምልመላ ወጣቶች የሚካተቱበትን አሰራርና የአባላት የአገልግሎት ዘመን ማራዘም እንዲሁም የመኮንኖች ምልመላ ከዚህ ቀደም ከሰራዊቱ አባላት ብቻ የነበረ ሲሆን፥ ይህ አሰራር ሰራዊቱን ከማዘመን አንጻር ክፍተት አለበት በሚል ምልመላው ሲቪሎችን እንዲያካትት በሚል ተካቷል።

ከአገልግሎት ዘመን ጋር በተያያዘም ከተራ ወታደር እስከ ከፍተኛ ማዕረግ መሻሻሎች እንዲደረጉ በአዋጁ ተካቷል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ ምክር ቤቱ በዛሬው በመደኛ ስብሰባው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅንም አጽድቋል።

በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ከተወያየበት በኋላ በ33 ተቃውሞና በ4 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን በክልሎች የአስተዳደር ወሰንና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚነሱ ችግሮችን ሀገር አቀፍ በሆነ እና በማያዳግም መልኩ ለመፍታት የሚያስችል ነው ተብሏል።

እንዲሁም ከወሰን አስተዳደር ጋር ተያይዞ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል የቅራኔ ምንጭ የሆኑ ችግሮችን ገለልተኛ በሆነ፣ ሙያዊ ብቃት ባለው እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ የሚያፈላልግ መሆኑም ተጠቅሷል።

ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሆነው ኮሚሽኑ አሳታፊ፣ ግልጽ፣ አካታችና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከአስተዳደር ወሰኖች፣ ራስን በራስ ማስተዳደር እና ከማንነት ጋር የተያያዙ ግጭቶችን እና መንስኤዎቻቸውን በመተንተን የመፍትሄ ሀሳቦችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለአስፈፃሚ አካላት የማቅረብ አላማ እንዳለውም ተገልጿል።(ኤፍቢሲ)