ፕሬዝዳንት ኦማር ጊሌ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በቀጠናው ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም አደነቁ

የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀጠናው ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም እንዲሁም የሚያደርጉትን የተሳካ የዲፕሎማሲ ስራ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በጅቡቲ ለሶስት ቀናት ሲሰጥ በቆየው የአምባሳደሮች እና የከፍተኛ ባለስልጣናት ስልጠና ላይ በመገኘት ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ዶክተር አብይ አህመድ በክልሉ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ቁርጠኛ አቋም ያላቸው፤ በእስካሁኑ ሂደትም አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ መሪ ናቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል እርቀ ሰላም እንዲወርድ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረው በጅቡቲና በኤርትራ መካከል ሰላም እንዲፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላደረጉት ከፍተኛ ስራም ፕሬዝዳንቱ ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀጠናውን በመወከል በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደረጉት ያለውን የተሳካ የዲፕሎማሲ ስራ ፕሬዝዳንቱ አድንቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ቀንድ የጎሳ እና የእርስ በርስ ግጭት የማይታጣበት ቀጠና መሆኑን ገልጸው ይህንኑ ወደ ሰላም ለመለወጥ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)