ኢንጂነር ታከለ ኡማ በመርካቶ እና አከባቢው ካሉ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ጋር ተወያዩ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በመርካቶ እና አከባቢው ከሚገኙ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከከተማ ገቢዎች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ከመርካቶ እና አከባቢዋ ከተውጣጡ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን ነጋዴዎች በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በንግድ ስርአት ህግ፣ በታክስ አሰባሰብ ስርአት፣ በህገ-ወጥ ንግድ እና ተያያዥ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ጥያቄ እና ቅሬታ አንስተዋል፡፡

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በውይይታቸው የአዲስ አበባ የኢኮኖሚ ማገር ከሆነው የመርካቶ እና አከባቢው የንግድ ማህበረሰብ ጋር በመገናኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ላይ ለደረሰው ኢ-ፍትሃዊ ተግባራት በሙሉ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
የነጋዴውን ቅሬታ ለመፍታት እና የታክስ አሰባሰቡን ዘመናዊ ለማድረግ አዲሱ አመራር ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመርካቶን ግብር ከፋይ መስማት፣ መደገፍ እና ማብቃት የከተማዋን እድገት ማፋጠን መሆኑንና ፍትሃዊ የንግድ ስርአት ለመፍጠር የከተማው አስተዳደሩ በቅርብ ቀን አዳዲስ አሰራሮችን ይፋ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡ (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)