ኦዲፒ ከኦነግ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ማክበሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

በኢትዮጵያ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲሰፍን የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ /ኦዲፒ/ ቁርጠኛ በመሆኑ ከኦነግ ጋር የተደረሰው ስምምነት ማክበሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አዲሱ አረጋ አስታወቁ።

የኦዲፒ ስራ አስፈፃሚ አባልና የገጠር ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ በጉዳዩ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ከዚህ ቀደም የተደረሰው ስምምነት በኦነግ በኩል በተደጋጋሚ እየተጣሰ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በበርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት የተገኘውን ለውጥ ወደ ኋላ እንዳይመለስና ኦነግ ስምምነቱን እንዲያከበር ኦዲፒ በትግዕስት በሩን ከፍቶ ይጠብቃል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው ኦዲፒ በለውጡ ቃል በገባው መሰረት የተለያዩ ማሻሻያዎችን እየተገበረ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

አዲስ የፖለቲካ ባህል እንዲመሰረት የመገናኛ ብዙሃን በነጻነት ለዴሞክራሲ ስርዓቱ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በነጻነት እንዲሰሩ ማድረግና እገዳዎችን ማንሳትን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቆም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ ስለመሆኑና ሌሎች ሪፎርም እየተተገበረ መሆኑንም አውስተዋል።

በሀገሪቱ ባለው የዴሞክራሲ ሁኔታ ምርጫቸውን የትጥቅ ትግል ያደረጉ እና በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሃይል በሀገር ውስጥ በነጻነት እንዲንቀሳስም ጥሪ ተደርጎ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የተለየ ስምምነት አለመደረጉን ያነሱት አቶ አዲሱ ከኦነግ ጋርም የተደረሰው ስምምነት የዓለም አቀፍ መስፈርትን መሰረት ያደረገና ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ከኦነግ ጋር በተናጠል የተደረሰ ልዩ ስምምነት የለም ነው ያሉት አቶ አዲሱ፡፡

በዚህም ከኦነግ ጋር የትጥቅ ትግሉን በማቆም ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግና መንግስትም ምቹ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች የሚል ቀዳሚ ስምምነት መደረጉንም አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፓርቲው ላይ የተሠጠው የሽብርተኝነነት ስያሜ እንዲነሳና የፀረ ሽብር ህጉም እንዲሻሻል ፓርቲውም በሀገር ውስጥ ሲንቀሳቀስ የሀገሪቱን ህግና ስርዓት ተከትሎ ህገመንግስቱን አክብሮ መሆን እንዳለበት ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።

የዴሞክራሲ ባህል ለመገንባትም ከጥሎ ማለፍ ያረጀ ፖለቲካ በመውጣት የትብብር ፖለቲካ መመስረትም አንዱ የስምምነቱ አካል ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በኤርትራ የነበሩ የኦነግ ታጣቂዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው መንግስት አስፈላጊውን ስልጠና ሰጥቷቸው ፍላጎታቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ፥ ከጸጥታ አካሉ ጋር መቀላቀልና እንዲሁም በተለያዩ የመንግስት ስራዎች ላይ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ማመቻቸትም የስምምነቱ አካል እንደነበርም ነው የገለጹት።

ሌሎች በሀገር ውስጥ የሚገኙ የኦነግ ታጣቂዎችም በተመሳሳይ ስምምነቱ በተደረሰበት ወቅት በሚሰላ በአስራ አምስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ወደ ካምፕ ገብተው ስልጠና በመውሰድ መሰል ድጋፎች እንዲደረጉላቸው ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበርም ነው ያሉት አቶ አዲሱ።

ይሁንና ኦዲፒ ይህንን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በኦነግ ስምምነቱን ያለማክበር ተደጋጋሚ ፈተናዎች እየገጠሙት ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የሚገኙ ታጣቂዎችም በስምምነቱ መሰረት በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ካለማስገባቱም በተጨማሪ በአምስት የክልሉ አካባቢዎች ሰራዊት መልምሎ በማሰልጠን የማደራጀት ስራ ውስጥ ገብቷል ሲሉ በመግለጫው ተናግረዋል፡፡

በዚህም በምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች የመንግስት መዋቅር የማፍረስ፣ ሚሊሻዎች ላይ ጥቃት የመፈጸም፣ የመንግስትና የግል ንብረቶችን የመዝረፍ እና የሰው ህይወት በታጣቂዎቹ እየጠፋ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሆኖም ኦዲፒ ሁኔታውን የለውጥ ሽግግር ባህሪ ነው ብሎ በማሰብ በትዕግስት እየተመለከተ መቆየቱንም ነው በመግለጫቸው ያስረዱት።

ስምምነቱ እንዲከበር በተደጋጋሚ ከኦነግ የፖለቲካ አመራሮች ጋር በጋራ በተደረገ ውይይት እየተፈጸመ ያለው ድርጊት አግባብ ያለመሆኑን የጋራ አቋም ተይዞ የነበረ ቢሆንም በታችኛው መዋቅር ግን እየተተገበረ እንዳልመጣም አብራርተዋል።

ይህም ኦዲፒ በኦነግ አመራሮች መካከል የጋራ አቋም አለመኖሩን መታዘብ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

አሁንም ቢሆን ኦዲፒ ከኦነግ ጋር የተደረሰውን ስምምነት እንደሚያከብር የገለጸ ሲሆን፥ የትጥቅ ትግልን አማራጫቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉ ከሆነ በሩ ክፍት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑም ሰላማዊ ትግል ለማድረግ በትጥቅ ትግል የነበሩ ከሰሜን ሸዋ፣ ከሆሮጉድሩ ወለጋ እና ከኢሉአባቦራ 112 ታጣቂዎች መመለሳቸውን አንስተዋል፡፡

ተመላሾቹም በሰላም ለመንቀሳቀስ ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ስምምነት በማድረግ መንግስት ተቀብሎ በችሎታቸውና በፍላጎታቸው መሰረት ወደ ስራ ለማሰማራት ዝግጁነቱን እንደገለጸላቸውም ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሃላፊነቱን እንደሚወጣም አያይዘው ጠቅሰዋል።(ኤፍቢሲ)