ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደርጉ ግለሰቦችንና የማህበራዊ ሚዲያ ቡድኖችን ኅብረተሰቡ እንዳይከተላቸው ጥሪ ቀረበ

የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ ውይይት ሲጀምር የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ባስተላለፉት መልዕክት ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደርጉ ግለሰቦችንና የማኅበራዊ ሚዲያ ቡድኖችን ኅብረተሰቡ እንዳይከተላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጉባኤው በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት የሰው ሕይወት እና ንብረት በጠፉበትና ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው በተፈናቀሉበት ወቅት የሚደረግ መሆኑን የገለጹት አፈጉባኤዋ የክልሉ ሕዝቦች መቻቻልን፣ መታገስን፣ ማስተዋልን፣ መፈቃቀርን፣ ማስታረቅን እና መታረቅን የሚያውቅ በመሆኑ ችግሮች እንደሚፈቱ ተናግረዋል።

‹‹በሕዝቦች መካከል የቆየው እሴት እስካሁንም የያዘን ወደፊትም የሚያስጉዘን የመልካም ግንኙነት መሠረት ነው›› ያሉት ወይዘሮ ወርቅሰሙ የቆየው የመልካም ግንኙነት እሴት በክልል ብቻ የታጠረ አለመሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ተምሳሌት፣ ዋልታና ማገር በመሆን ለዴሞክራሲያዊ አንድነት መሰዋዕት የሚሆን ሀገር ወዳድ እንደሆነም በንግግራቸው ዳስሰዋል።

ይሁን እንጅ የአገር ግንባታው ሂደቱን ፈታኝ ያደረጉ የሰላም እጦቶች እና ሕግ ያለመከበር ሕዝቡን እና መንግሥትን እረፍት መንሳታቸውን ጠቅሰዋል። በክልሉ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖችና አካባቢው ማንነትን ሽፋን ተደርገው የተቀሰቀሱ ግጭቶች ከአንድ ማኅፀን በተፈጠሩ እህትና ወንድም ነዋሪዎች ላይ የተቃጣ ሞት እና መሰደድ ያስከተለ ተግባር እንደሆነም አፈ-ጉባኤዋ አስታውቀዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በኅብረተሰቡ የተጀመሩ ምክክሮች እና ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳባለቸው ያሳሰቡት ወይዘሮ ወርቅሰሙ ‹‹ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደርጉ ግለሰቦችንና የማኅበራዊ ሚዲያ ቡድኖችን ማደናገራቸው እንዳይቀጥል ሕዝቡ እኩይ ተግባራቸውን ተረድቶ መደበቂያ እና እርካብ ሊነፍጋቸው ይገባል›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በምክር ቤቱ የዛሬ ውሎ የክልሉ የሰላም እና ደኅንነት ቢሮ የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ውይይት ተደርጎበት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡

በቀጣይ ቀናት ደግሞ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ ስልጣን እና ተግባር ማሻሻያ ዓዋጅ እና የምሁራን መማክርት ማቋቋሚያ ቻርተርን ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ እና ልዩ ልዩ ሹመቶች እንደሚሰጥ ይጠበቃል። (አብመድ)