በአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ ክስ ተመሰረተ

የአማራ ክልል ፀረ ሙስና አቃቤ ህግ በአቶ ረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ ክስ መሰረተ።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት በጥረት ኮርፖሬት ላይ ፍተኛ የሀብት ብክነት በማስከተል የተጠረጠሩትን አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳን ጉዳይ ተመልክቷል።

የሁለቱን ተጠርጣሪዎች ክስ በአንድ ላይ ለማዳመጥ የተሰየመው ችሎቱ፣ የክሱ ዝርዝር ጉዳይ በትናንትናው ዕለት ለተከሳሾቹ በፅሑፍ መድረሱን ገልጿል።

ተከሳሾች በበኩላቸው የክስ መዝገቡ በትናንትናው ዕለት 12 ሰዓት ላይ እንደደረሳቸውና ገፁ 1 ሺህ 9 መሆኑን በመግለፅ በአግባቡ አንብበውና ተገንዝበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ ጠበቃ ማቅረብ ባለመቻላቸው በውጭ ጠበቃ አቁመው በፕላዝማ እንዲከታተሉ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲፈጥርላቸው ጠይቀዋል።

ይህ ካልሆነ ደግሞ የህግ አማካሪ ባለሙያ እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ሃሳብ ያዳመጣው ፍርድ ቤቱም ተከሳሾች ጠበቃቸውን ማቆም ይችሉ ዘንድ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ትብብርና ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ያቀረቡትን አቤቱታ ግምት ውስጥ በማስገባት በክሱ ላይ ያላቸውን ሃሳብ ለማዳመጥ ለሚያዚያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

(ምንጭ፡- ኤፍቢሲ)