የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዝዳንት ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

የኢኳቶሪል ጊኒ ፕሬዚዳንት ኦቢያንግ ኑጌማ ማሶጎ አዲስ አበባ ገብተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከአፍሪካ ህብረት አመራሮች ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

በነገው ዕለትም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘውን የፆሬ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያን እንደሚጎበኙ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከዚህ ባለፈም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የስደተኞች ስምምነት የተፈረመበትን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ በአፍሪካ ህብረት በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ይሳተፋሉ።