በዘንድሮው ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል 94 በመቶዎቹ ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸው ተገለጸ

በዘንድሮው ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል 94 በመቶዎቹ ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸው ተገለጸ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የመንግስትን የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሰኔ 24/ 2011 አቅርበዋል።

በአገሪቷ ከለውጡ በፊት ከነበረውን የተፈናቃይ ቁጥር ጨምሮ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ተፈናቃዮች በዘንድሮው ዓመት የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ከአጠቃላይ ተፈናቃዮች ውስጥ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል።ይህም ከአጠቃላዩ ተፈናቃዮች 94 በመቶ የሚሆኑት ወደ ቀዬያቸው ተመልሰዋል።

ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች እንደተፈናቀሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

ከተፈናቀሉት ዜጎች ውስጥም 400 ሺህ የሚሆኑት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተፈጠረ ችግር የተፈናቀሉ ነበሩ ብለዋል፡፡

ከተፈናቃዮቹ መካከል 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ያክሉ በሚኖሩበት ክልል የተፈናቀሉ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ 800 ሺህ ደግሞ ከሚኖሩበት ክልል ወደ ሌላ ክልል የተፈናቀሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ለቀሪዎቹ ተፈናቃዮቹ የሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስና ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንዲሁም ለማቋቋም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ግጭት ማስቆምና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተሰራ ስራ በተለያዩ ወንጀሎች ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 48 የሽብር ቡድን አባላት፣ ብሄርን መሰረት ባደረገ ጥቃት የተጠረጠሩ 799 ተጠርጣሪ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ኢንዲሁም በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ወንጀሎች ከተጠረጠሩ 35 ግለሰቦች ውስጥ 34ቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር 64 ግለሰቦች፣ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ደግሞ 51 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡