በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት አውሮፕላን ተከስክሶ የ10 ሰዎች ህይወት አለፈ

በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት አንድ አነስተኛ አውሮፕላን ተከስክሶ በውስጡ ተሳፍረው የነበሩ 10 ሰዎች በሙሉ ህይወታቸው አለፈ።

አነስተኛ አውሮፕላኑ አዲስን ከተሰኘ አየር ማረፊያ እንደተነሳ ከአየር ማረፊያው ሳይርቅ ከአውሮፕላን ማቆሚያ ህንጻ ጋር ተላትሟል።

ባለ ሁለት ሞተሩ ቢኢ-350 ኪንግ ኤር የተሰኘው አውሮፕላን በአየር ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ መቆየቱ ተሰምቷል።

በደንገት አቅጣጫ በመቀየር ከህንጻው ጋር መላተሙ እና ከፍተኛ እሳት መከሰቱን የአከባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ ቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል።

የአየር ማረፊያው ምክትል ዳይሬክተር ደርሲ ኑኡዚል አውሮፕላኑ በሃገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 3 ሰዓት እንደተነሳ እና ወደ ፍሎሪዳ የሚያቀና ነበረ ብለዋል።

አደጋው እንደተከሰተ የህይወት አድን ሰራተኞች በስፍራው ቢደርሱም በህይወት ማትረፍ የቻሉት ተሳፋሪ ግን አልነበረም።

ባለስልጣናት የተጎጂ ቤተሰቦችን አርድተው ስላልጨረሱ የሟቾችን ማንነት ለመገናኛ ብዙሃን እስካሁን አላሳወቁም።

አውሮፕላኑ ከህንጻው ጋር የተላተመበት ቦታ በህንጻው አካል ላይ ትልቅ ክፍተትን ፈጥሯል። አደጋው ሲከሰት በህንጻው ውስጥ ሰው አልነበረም ተብሏል።

ማንነታቸው ያልተገለጹ ምንጮች ለሲቢኤስ የዜና ወኪል እንደገለጹት አውሮፕላኑ አደጋው ያጋጠመው በሞተር መበላሸት ነው ብለዋል። ምንም እንኳ ይህ በሚመለከታቸው ባለስልጣናት ባይረጋገጥም።

የአሜሪካ ብሄራዊ የትራንስፖርት እና ደህንነት ቦርድ አደጋውን እየመረመርኩ ነው ብሏል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)