ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ስምምነት ላይ ለደረሱት ለሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት፣ ለተቃዋሚ ሀይሎች እና ለሀገሪቱ ህዝቦች የደስታ መልክት አስተላለፉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ስምምነቱ በሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገሪቱ የፖለቲካ ሀይሎች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው አምሳደር መሀመድ ድሪር እና መሀመድ ሀኬን አል ላባትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣዩ ጊዜ ለሱዳን የሰላምና የብልፅግና እንዲሆን ምኞታቸው አስተላልፈዋል፡፡
የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት እና ተቃዋሚ ሃይሎች ስልጣን ለመጋራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት፣ ጥምር ተቃዋሚ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ስልጣን ለመጋራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በስምምነቱ መሰረትም ሃገሪቱ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ከወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት እና ከተቃዋሚዎች በተውጣጣ የጋራ አስተዳደር አማካኝነት የምትመራ ይሆናል።
ለዚህም በጋራ ሉዓላዊ ምክር ቤት መመስረት የሚያስችላቸው ስምምነት ላይ መድረሳቸውም ነው የተነገረው፡፡
በሉዓላዊ ምክር ቤቱ ውስጥ አምስት መቀመጫዎች ለወታደራዊ ሃይል፣ አምስት መቀመጫዎች ለሲቪሎች፣ እና ሌሎች መቀመጫዎች ደግሞ ወታደራዊ ተሳትፎ ለነበራቸው ከሲቪሉ ለተውጣጡ አካላት ይሰጣል ተብሏል፡፡
ተደራዳሪዎቹ በቅርብ ጊዜያት በሀገሪቱ በተከሰቱ ግጭቶች የደረሱ ጉዳቶች ላይ ግልጽና ከወገንተኝነት የጸዳ ምርመራ እንዲካሄድም ስምምነት ላይ ደርሰዋል ነው የተባለው፡፡