ከልክ ያለፈ ውፍረት ለካንሰር በሽታ እንደሚያጋልጥ ጥናት አመላከተ

ተገቢ ያልሆነና ከልክ ያለፈ ውፍረት ሲጋራ ከማጨስ በላይ ለካንሰር በሽታ የሚያጋልጥ መሆኑን አንድ ጥናት አመላክቷል።

በብሪታኒያ በካንሰር በሽታ ላይ ምርምር የሚያደርግ ተቋም ይፋ ባደረገው ጥናት ከልክ በላይ ውፍረት  ለጉበት፣ ኩላሊት፣ ደም ስር እና ለማህፀን ካንሰር በሽታ ያጋልጣል ተብሏል፡፡

በዚህ መሰረትም ከልክ በላይ የሆነ ውፍረት ሲጋራ ከማጨስ ጋር ሲነፃፀር ለካንሰር በሽታ የማጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑም ነው በጥናቱ የተመላከተው።

ተመራማሪዎች ጥናቱ የተካሄደው ወፍራም ሰዎችን ለመውቀስ ሳይሆን ተገቢ ያልሆነ ውፍረት ሲጋራ ከማጨስ በላይ ለካንሰር በሽታ የሚያጋልጥ መሆኑን ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ብለዋል።

ከመጠን ባለፈ ውፍረት በሚመጣ የክብደት መጨመር ምክንያት በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለካንሰር በሽታ እንደሚጋለጡ ተገልጿል።

በብሪታኒያ ሲጋራ ማጨስ ዜጎችን ለካንሰር በሽታ ከማጋለጥ አንፃር የመጀመሪያው ሲሆን፣ ተገቢ ያልሆነ ውፍረት ደግሞ ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል።

ይሁን እንጅ በአሁኑ ወቅት ተገቢ ባልሆነ ውፍረት ምክንያት ለካንሰር በሽታ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ በጥናት ተመላክቷል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)