ከሲቪል ማህበራት ተቋማት አመራሮች ጋር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ውይይት ተካሄደ፡፡
በውይይቱ አመራሮቹ በሀገሪቱ እየተካሄደ በሚገኘው ለውጥ ሂደት የተመዘገቡ ውጤቶች እና ችግሮችን አንስተዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ በሀገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘውን ለውጥ ማስቀጠል እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች መልካም አስተዳደርን፣ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማሻሻል እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን ድጋፍ እንዲያደርጉ በውይይቱ ማገባደጃ ለሲቪክ ማህበራት አመራሮች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የተካሄደው ውይይት ከዚህ በፊት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያካሄደው ውይይት አካል ነው ተብሏል፡፡
የውይይቱ ዋነኛ አላማ ባለድርሻ አካላት መንግስት እያካሄዳቸው ባሉ ለውጦች ላይ ሊኖራቸው በሚችለው ተሳትፎ ላይ ማተኮሩ ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ ላይ ባለደርሻ አካላቱ ሊኖራቸው በሚችለው ሚናም ለመምከር ያለመ መሆኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡