በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባል – የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 6 ፣ 2008 (ዋኢማ) – በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፍታት እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ።

ከሰሞኑ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች በተቀሰቀሰው ሁከትና ግርግር በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ የሚታወቅ ነው።

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤም ይህን በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰውን ሁከትና ግርግር አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።

አለመግባባቱ የወለደው ሁከትና ግርግር ሰላም ወዳዱን የህብረተሰብ ክፍል የእለት ተእለት እንቅስቃሴውን የሚያስተጎጉል እንደሆነም ነው በመግለጫው የተነሳው።

የጉባኤው የበላይ ጠባቂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፥ ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ቀርበው በውይይት እና ምክክር ምላሽ ቢያገኙ መልካም መሆኑን ተናግረዋል።

ምዕመኑ በየቤተ እምነቱ ለሀገሪቱ ሰላም ተግቶ ሊጸልይ ይገባል ያሉት ብፁዕነታቸው፥ በሰውና በንብረት ላይ በደረሰው ድንገተኛ አደጋም በሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስም የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን ገልጸዋል።

የጉባኤውን መግለጫ ያቀረቡት የጉባኤው የቦርድ አባል አባ ሀይለማሪያም መለሰ፥ የጉባኤው አባላትና የሀገሪቱ የሀይማኖት መሪዎች የሀገሪቱና የህዝቡ ሰላም በእጅጉ ያሳስበናል ብለዋል።

ምዕመኑም በመከባበር ላይ የተመሰረተ የአብሮነት እሴቶችን ማጎልበት እንደሚገባው ጠቅሰው፥ የየቤተ እምነቱ የሀይማኖት መሪዎችና ሰባኪያነ ወንጌልም ሰላምን አብዝተው ሊሰብኩ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ለሀገርና ለወገን የሚበጁ ጥያቄዎችን ማንሳት መሰልጠን ነው ያሉት አባ ሃይለማሪያም፥ ምላሹን በልበ ሰፊነትና በትዕግስት መጠበቅ ተገቢነት አለው ሲሉም ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

አያይዘውም በተለያዩ የመንግስት የስራ ሀላፊነት ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች የተጣለባቸውን፥ ሀገርና ህዝብን የመምራት ከባድ አደራ በአገልጋይነት መንፈስ መወጣት እንደሚገባቸውም አንስተዋል።

ጉባኤው የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎችና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ወገኖች ሁሉ፥ ህዝብን በማረጋጋትና በመምከር ሀገራዊና ሀይማኖታዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝቧል።

በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች የሚነዙ ሀሰተኛ ወሬዎችን ህዝቡ አምኖ ከመቀበሉ አስቀድሞ መመርመር ይገባዋልም ብሏል።(ፋብኮ)