ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ1ነጥብ6 ቢሊየን ብር ግንባታ እያከናወነ ነው

የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ1ነጥብ6 ቢሊየን ብር ልዩ ልዩ የኮንስትራክሽን ስራዎች  እያገባደደ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕረዚዳንት አስታወቁ ፡፡

ፕረዚዳንቱ ዶክተር ዛይድ ነጋሽ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተበት ከህዳር 26 ቀን 2004 ዓም አንስቶ የተለያዩ የህንጻ ግንባታዎች በማከናወን የመማር ማስተማር ሂደቱን በማጠናከር ላይ ይገኛል ፡፡

እንደ ዶክተር ዛይድ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው የህንጻ ግንባታ ሲጀምር 12 ብሎክ ብቻ የነበሩት ሲሆን አሁን ግን ከ190 በላይ ብሎኮች ተገባደው ለተለያዩ አገልግሎቶች ብቁ ሆነዋል ፡፡

የህንጻ ስራዎቹ የመሰረተ ልማት ፣ የመማር ማስተማሪያና የቢሮ አገልግሎት ሰጪ ያካተቱ መሆናቸውን አመልክተዋል ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ካሉት ሁለት ካምፓሶች እስካሁን በዋናው ካማስ እየሰሩ ሲሆን ፤በሁለተኛው አዲስ ካምፓስ ደግሞ 33 ብሎኮች ግንባታ ስራው ተጠናቀው በ2009 ዓመተ ምህረት አጋማሽ ላይ ስራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል ፡፡

በአጠቃላይ ለኮንስትራክሽን ስራው እስካሁን 1ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቁመዋል ፡፡

ከዚሁም ውስጥ ዩኒቨርሲቲው በ2008 ዓመተ ምህረት ለግንባታ፣ለውስጥ ቁሳቁስ ሟሟያ እና ሌሎች ወጪዎች 497 ሚሊየን መድቦ 99 ነጥብ 5 በመቶ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአራት ኮሌጆች በ13 የትምህርት ዓይነት የትምህርት ዓይነቶች በ960 ተማሪዎች ስራ መጀመሩን ያስታወሱት ፕረዚዳንቱ ፤አሁን በመደበኛ፡ በክረምትና በማታ በ46 የትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪና የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች ከ18ሺ በላይ ተማሪዎች ለማስተናገድ መቻሉን አስታውቀዋል ፡፡