የአፍሪካ ልማት ፎረም በፍልሰት ላይ ያተኩራል

ኢትዮጵያ ከሦስት ወራት በኋላ የምታስናግደው 10ኛው የአፍሪካ ልማት ፎረም በፍልሰት ዙሪያ እንደሚያተኩር የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ አብደላ ሃምዶክ ገለጹ።

''ፍልሰትና የአፍሪካ ሽግግር'' በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ ፎረም ላይ የአፍሪካ እውቅ የፍልሰት ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ተገናኝተው ይወያያሉ።

ኮሚሽኑ ከአፍሪካ ኅብረትና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር የሚያዘጋጀው ፎረም የንግዱ ማሀበረሰብ፣የሲቪል ማህበራትና የፖለቲካ አመራሮች የሚገናኙበት መድረክ  እንደሆነም አመልክተዋል።

በተለይም የአፍሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ፍልሰት የአፍሪካ ሽግግር ለመደገፍ በጉዳዩ ላይ አማራጭ ፖሊሲዎች ለማዘጋጀትና አጋርነታቸውን የሚያጠናክሩበት ይሆናል ነው ያሉት።

ዓለም አቀፍ ፍልሰት አህጉሪቷን ለማልማት በተለይ ደግሞ ማህበራዊ ዋስትና ማጠናከር፣ ሰላምና ጸጥታን ማስፈን እንዲሁም እያደገ ላለው የህዝብ ቁጥር የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ባለው ፋይዳ ላይም ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።   

የፍልሰት ጉዳይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ትልቅ የመከራከሪያ ጉዳይ መሆኑን ያስታወሱት ሚስተር ሃምዶክ፣ በተለይ አፍሪካውያን ስደተኞች የሚጠይቁት ጥገኝነትና ከወንጀል ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።

በፎረሙ ላይ የአገሮች መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮች፣የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣የትምህርት ተቋማትና የግል ተቋማት ተወካዮች ይገኙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ክፍል አስታውቋል።(ኢዜአ)